በሊጉ የመጠናቀቂያ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ዙሪያ በተጫዋቾች እና በክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔዎች ተላልፈዋል።
የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው ቅዳሜ በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት መጠናቀቁ ይታወሳል። በእነኚህ የሊጉ የመጨረሻ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የሊግ አክሲዮን ማህበሩ የውድድር አመራር እና ስነስርዓት ኮሚቴ ታዩ ያላቸውን የዲሲፕሊን ጥሰቶች ከመረመረ በኋላ በተጫዋቾች እና በክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል።
በተጫዋቾች እና በቡድን አመራሮች ዙሪያ በተሰጡ ውሳኔዎች የአርባምንጭ ከተማው ተከላካይ በርናንድ ኦቼንግ እና የመቻሉ አማካይ ግሩም ሃጎስ በተለያዩ ጨዋታዎች በተመለከቱት 5 ቢጫ ካርዶች 1 ጨዋታ እንዲታገዱ እንዲሁም አንድ ሺ አምስት መቶ ብር እንዲከፍሉ ሲወሰን ፣ የአርባምንጭ ከተማው አጥቂ አህመድ ሁሴን ክለቡ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የራሱን ክለብ ደጋፊዎች በምልክት አፀያፊ ስድብ በመሳደቡ ሪፖርት ሶስት ጨዋታ እንዲታገድ ሦስት ሺህ ብር እንዲከፍል ፥ የባህርዳሩ አደም አባስ በበኩሉ ወላይታ ድቻን ክለቡ ሲረታ ብቸኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ሃይማኖታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ በመልበሱ ተጫዋቹ ሶስት ሺህ ብር እንዲሁም ክለቡ ደግሞ አስር ሺህ ብር በድምሩ አስራ ሦስት ሺህ እንዲከፍሉ ሲደረግ ፥ የወልቂጤ ከተማው ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ታዳሙ ከአዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ በጨዋታ ወቅት አወዳዳሪ አካልን በመሳደባቸው አራት ወር እንዲታገዱ እና በተጨማሪም አስር ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡
በክለብ ደረጃ አርባ ምንጭ ከተማ ከ ሃዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ደጋፊዎቹ የጨዋታ አመራሮችን አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት ደጋፊዎቹ ተመሳሳይ ጥፋት 2 ጊዜ አጥፍተው ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው አንድ መቶ ሺህ ብር እንዲከፍል ፥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋን በገጠመበት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የተቀያሪ ተጫዋቾች መቀመጫ ጣሪያ ላይ ጉዳት ስለማድረሳቸው ሪፖርት የተደረገ በመሆኑም ክለቡ የተጎዳውን ንብረት እንዲያሰራ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የማሰሪያ ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡