\”ክለቦቻችንን እንታደግ\” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

ለመቐለ 70 እንድርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ የተዘጋጀውን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በሸራተን አዲስ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻውን ያዘጋጀው ኢ ዋይ ፕሮዳክሽን ባለቤት ጋዜጠኛ ኤፍሬም የማነህ እንዲሁም የማርኬቲንግ ባለሙያው አቶ መድሃኔ ዘካሪያስ፣ የመቐለ 70 እንደርታ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ተ/ኃይማኖት፣ የወልዋሎ ዓ/ዩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሚካኤሌ አምደመስቀል እና የስሑል ሽረ የቦርድ አባል አቶ ተመስገን ገ/ህይወት ተገኝተዋል።

\"\"

በቅድሚያ ጋዜጠኛ ኤፍሬም \”በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሀገር ደረጃ ተሳታፊ የነበሩ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በብሄራዊ ቡድን ታላቅ ሚና ያላቸው ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች (መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩንቨርስቲ እና ስሑል ሽረ) ባለፉት ሦስት ዓመታት ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት ምክንያት ክለቦቹ ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል። እነዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፕሪምየር ሊጉ ድምቀት እና መነቃቃትን ፈጥረው የነበሩ ክለቦች ፈርሰው እንዳይበተኑ ለማድረግ የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ነው።\” በማለት ንግግራቸውን ከጀመሩ በኋላ የትግራይ ክልል ስፖርትን ለማነቃቃት እና ህዝቡ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት የስነ ልቦና ቀውስ በቶሎ ማገገም እንዲችል ማድረግ እንዲሁም ተቀዛቅዞ የነበረውን የስፖርት ውድድር መንፈስ መልሶ ማነቃቃት የሚሉ ዓላማዎችን ሰንቆ የተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እንደሆነ አመላክተዋል።
\"\"
በሀገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይ ከዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች እና ሌሎች አካላት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የመሰብሰብ ግብ እንደያዘ የተነገረው ይህ ዘመቻ ለ60 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከዛሬው የጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ በአዲስ አበባ ወንድማማቾች ፓርክ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐብይ አህመድ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ እንግዶች በሚገኙበት የመክፈቻ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል። ከዛም በጥምር የጎ ፈንድ ሚ አካውንት ተከፍቶ ዘመቻው የሚደረግ ሲሆን ጎን ለጎንም የኤስ ኤም ኤስ እና የሀገር ቤት የገንዘብ አሰባሰብ ስርዓቶች (በባንክ) ዘመቻው ተደርጎ የገቢ አሰባሰሰቡ ከ60 ቀናት በኋላ መቐለ ላይ እንደሚቋጭ ተመላክቷል። በመሐል ስፖርት በትግራይ ከጦርነቱ በፊት እና በኋላ ያለበትን ሁኔታ የሚያስቃኝ አጭር ዶክመንታሪ ፊልም እንደሚዘጋጅ እንዲሁም ስፖርት ጦርነትን ከመቀልበስ እና ሰላምን ከማስፈን አንጻር የዓለም ተሞክሮ ምን ይመሰላል የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ በመቐሌ ዩንቨርሲቲ መምህራን አቅራቢነት ከስፖርት ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም ተጠቅሷል።

\"\"

በመቀጠል መድረኩት የተረከቡት የሦስቱ ክለብ ተወካዮች ሲሆኑ አመራሮቹም በጦርነቱ በክልሉ የደረሰውን ውድመት በመጥቀስ በይፋ በገንዘብ አሰባሰብ ጉዳይ ፍቃድ የሰጡት ለኢ ዋይ ፕሮዳክሽን እንደሆነ በየተራ ተናግረዋል። በተለይ የመቐለ 70 እንደርታ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ኢ ዋይ ፍቃድ ያገኘበትን መንገድ ከጥንስሱ ጀምረው አብራርተዋል። የወልዋሎው ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሚካኤሌ ጨምረውም በክለባቸው ስም ገቢ ለመሰብሰብ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተቋማት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
\"\"
በዘመቻው ከተሰበሰበው 500 ሚሊዮን ብር ሦስቱ ክለቦች እያንዳንዳቸው 30% ሲያገኙ ቀሪውን 10% ደግሞ ኢ ዋይ ፕሮዳክሽን እንደሚያገኝ ተጠቁሟል። ከገቢ ማሰባሰቡ ጋር ተያይዞም ይህ ዘመቻ ሦስቱን ክለቦች ቢመለከትም በዙር ሁለት ሌሎች በታችኛው ሊግ የሚሳተፉ የክልሉ ክለቦችን የሚደጉም ሌላ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እንደሚደረግ ተገልጿል። የክልሉን ክለቦች ለመደገፍ ሌላ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ የጀመረውን ሌላ ተቋም በተመለከተ ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ወደ መድረኩ የተሰነዘሩ ሲሆን ከስሑል ሽረ ውጪ ያሉት ሁለቱ ክለቦች ምንም አይነት እውቅና ለሌላ ተቋም እንዳልሰጡ ሲያስረዱ ተደምጧል።

\"\"

በመጨረሻ የመቐለ 70 እንደርታ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ይርጋ እንዲሁም የወልዋሎ ዓ/ዩ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ በመጨረሻ የማጠቃለያ ንግግር አድርገው መላው ኢትዮጵያዊያን ይህንን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እንዲቀላቀል ጥሪ በማስተላለፍ መግለጫው ተጠናቋል።