ኢትዮጵያዊቷ አሰልጣኝ እና ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዓይ በያዝነው ሳምንት ወደ ላይቤሪያ አምርታ የሀገሪቱን ዕንስት ብሔራዊ ቡድን በይፋ ትረከባለች።
እግር ኳስ መጫወትን ካቆመች በኋላ ወደ ስልጠናን ዓለም ጎራ በማለት በወንዶች እግር ኳስ የአሰልጣኝነት ህይወቷን ጀምራለች። በመቀጠል ግን የቅዱስ ጊዮርጊስን የሴት ቡድን ጨምሮ የኢትዮጵያ ወጣት እንዲሁም ዋናውን የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በኦሎምፒክ እና በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ በዋና አሰልጣኝነት መምራቷም ይታወሳል። ኢትዮጵያን ወክላ እንስት የካፍ ኢንስትራክተር በመሆን ያለፉትን ዓመታት እየሰራች የምትገኘው እና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የአቃቂ ቃሊቲን የሴቶች ቡድን አሰልጥና የነበረችው አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ባሳለፍነው ሳምንት የላይቤሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለሁለት ዓመት እየታየ በሚጨመር አንድ ዓመት እዚሁ አዲስ አበባ በኦንላይን የኮንትራት ፊርማዋን አኑራለች። ከሁለት ቀናቶች በኋላ ወደ ስፍራው ለማምራት የጉዞ ትኬት እየጠበቀች የምትገኘው አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ስላገኘችው ዕድል ፣ ስለ ውል ስምምነቷ እና መሰል ጉዳዮች አጭር ማብራሪያን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አድርጋለች።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ በአህጉር ደረጃ የሚገኝን የሴት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርገሽ ስትሾሚ የመጀመሪያ ነሽ እና ምን ተሰማሽ …?
\”በጣም ትልቅ ዕድል ነው ብዬ ነው የማስበው። ይህ ማለት የመጀመሪያ መሆን ምናምን ሳይሆን ይሄ ዕድል ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች አይችሉም ምንም አያውቁም በሚባልበት ጊዜ ማግኘቴ ብዙ አሰልጣኞች እንደሚችሉ ቦታው ላይ እንደሚመጥኑ የሚያሳይ ነው ብዬ ነው የማስበው። ሁለተኛው እነዚሁ አሰልጣኞች ደግሞ ወጥተን ማሰልጠን እንችላለን የሚል ሁሉም ጋር ግንዛቤው እንዲያድር በር የሚከፍት ነው ስለዚህ በጣም ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ። በዛው ልክ ደግሞ ትልቅም ኃላፊነት ነው ያለው። ማለት እዛ ሄጄ የግድ ሊሳካለኝ ይገባል ቀጥሎ ያሉት አሰልጣኞች አቅማቸውን እንዲያሳዩ የግድ ዕድሉን ልጠቀምበት ይገባል እና ኃላፊነትም ይሰማኛል ደስታ ብቻም ሳይሆን።\”
ተጫዋች ነበርሽ ፤ እስከ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ደርሰሻል ፤ ኢንስትራክተርም ነሽ ፤ አሁን ደግሞ የውጪ ብሔራዊ ቡድን መያዝ ችለሻል። የእግር ኳስ ጉዞሽን እንዴት ታይዋለሽ?
\”የደረስኩባቸው ሳይ ብዙ ተጉዣለሁ ብዬ ነው የማስበው ፤ ግን ካሳለፍኩት ውጣ ውረድ አንፃር ያለፍኳቸውን ችግሮች ሳይ ያው ብዙ ሰው እነርሱን ስለማያይ አሁን ያለውበት ደረጃ ይገባኛል ብዬ ነው የማስበው። ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። በፍጥነት ነው ፤ ማለት አንድ አስራ ሁለት ዓመት ስልጠና ከጀመርኩኝ እና እያንዳንዱን ዓመት በአግባቡ ተጠቅሜያለሁ። ከእግዚአብሔር ጋር እርሱም እዚህ አድርሶኛል። ሌላው ደግሞ ውጣ ውረድ ማየቴ በእግር ኳስ ህይወቴ ብዙ ነገሮችን ማየቴ ረድቶኛል ብዬ ነው የማስበውና በጣም ደስተኛ ነኝ።\”
በእግር ኳስ ረዘም ያሉ ዓመታትን አሳልፈሻል ፣ በመጨረሻም ከሀገርሽ አልፈሽ በአህጉር ደረጃ ብሔራዊ ቡድን ይዘሻል ሒደቱ ምን ይመስላል ፣ በምን አይነት መንገድ ነበረ የላይቤሪያን ዕድል ያገኘሽው ፣ የነበረሽ ግንኙነት ምን ይመስላል ? ምንስ ፈጠረብሽ ?
\”የግንኙነት ጊዜዬ ትንሽ ረዘም ይላል። የመጀመሪያ መልዕክት ነው ያገኘሁት ኮርስ እየሰጠው ነበርና ፣ ኮርሱን ጨርሼ ስልኬን ቼክ ሳደርግ መልዕክት ተመለከትኩ \’የላይቤሪያን ብሔራዊ ቡድንን እንድታሰለጥኚ እንፈልጋለን ፍቃደኛም ከሆንሽ ኮንታክት አድርጊን\’ ይላል። በወቅቱ ትንሽ ግራ ገብቶኝ ነበር። ይሄ ነገር እውነት ነው ምንድነው የሚል ነገር ነበርና ወዲያውኑ ኮርስ እየሰጠው ነው ነገር ግን በዚህ ሰዓት ነፃ ስለሆንኩኝ ልታገኙኝ ትችላላችሁ የሚል መልዕክት ላኩላቸው ወዲያውኑ ባልኩት ሰዓት ደወሉልኝ ከአንድ ሰዓት በላይ ነው ኢንተርቪው የነበረው ከእዛ ሲቪዬን እንድልክ አደረጉ ከዛም ቀጥታ የእኔ ኤጀንት አክብረት ተመስገን እንዲያገኙ አደረኩኝ በእርሷ በኩል ነው ሁሉም ነገር ያለቀው ማለት ነው። በዚሁ አጋጣሚ እርሷንም በደንብ አመሰግናለሁ።\”
የላይቤሪያ ብሔራዊ ቡድንን ለስንት ዓመት ነው ለማሰልጠን የፈረምሽው? የውል ሒደቱ ምን ይመስላል ?
\”ውሉ 2+1 ነው የሚባለው ፤ ሁለት ዓመት ነው ኮንትራቱ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ሁለታችንም ደስተኞች ከሆንን በስራው ላይ አንድ ዓመት ጭማሪ ይኖረዋል ማለት ነው። ወይ እኔ አልያም እነርሱ ደግሞ ደስተኛ ካልሆኑ ሁለት ዓመት ላይ ውሉ ይቋረጣል ማለት ነው። አንድ ዓመት ፕላሱ እንደምናሳየው ፐርፎርማንስ ይወሰናል። በአጠቃላይ ሦስት ዓመት ነው ግን ሁለት ዓመት የፀና ሆኖ አንድ ዓመቱ ደግሞ እንደማሳየው አቅም የሚጨመር ይሆናል።\”