በአፍሪካ መድረክ ላለባቸው ውድድር በቅርቡ ቅድመ ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮኖች የአንድ ተጫዋቻቸውን ውል አራዝሟል።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ዋንጫ ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ መድረክ እና ለቀጣይ አመት ራሱን አጠናክሮ ለማዘጋጀት ወደ ዝውውሩ እንቅስቃሴ እየገባ ይገኛል። አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ከመቀላቀሉ አስቀድሞ በያዝነው ዓመት ውላቸው የተጠናቀቁ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ዳግመኛ በቡድኑ ለማቆየት ድርድር እያደረገ ሲገኝ በዛሬው ዕለት አማካይ ናትናኤል ዘለቀን ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በቡድኑ ለማቆየት ከስምምነት መድረሱን አውቀናል።
ከክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ጀምሮ ከ2002 ያለፉትን አስራ ሦስት ዓመታት በፈረሰኞቹ ቤት የቆየው ናትናኤል ስድስት የሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ሲሆን የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋችች መሆንም ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣዮቹ ጊዚያት ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን በክለቡ የማቆየት ስራ ከመስራቱ ባሻገር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ማስፈረም እንደሚገባ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።