ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ በአሜሪካ በሚደረገው \”ግራንድ አፍሪካ ረን\” ውድድር የመወዳደሪያ ትጥቆችን ለማቅረብ ስምምነት ፈፀመ።
ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከሀገር አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ምርቶቹን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። አሁን ደግሞ በሀገረ አሜሪካ በሚደረገው እና ኖቫ ኮኔክሽንስ በሚያዘጋጀው \”ግራንድ አፍሪካ ረን\” ውድድር በብቸኝነት የመወዳደሪያ ትጥቆችን ለማቅረብ በዛሬው ዕለት ስምምነት ፈፅሟል።
ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የጎፈሬ ማርኬቲንግ ቢሮ በተደረገው ስምምነት ላይ በርካታ የብዙሃን መገናኛ አባላት የተገኙ ሲሆን ስምምነቱን ለመፈፀም እና ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት ደግሞ የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም በታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ማኔጅመንት መምህር፣ በአሜሪካ በሚገኙ የስፖርት ድርጅቶች ውስጥ በአማካሪነት የሚሰሩት እና የኖቫ ኮኔክሽን ሥራ-አስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር ጋሻው አብዛ ተገኝተዋል።
በቅድሚያ ሀሳባቸውን የሰጡት ዶ/ር ጋሻው ለአምስተኛ ጊዜ ስለሚደረገው \”ግራንድ አፍሪካ ረን\” ውድድር መጠነኛ ገለፃ ካደረጉ በኋላ በውድድሩ የሚሳተፉት ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው ባህላቸውን ስለሚያስተዋውቁ በሀገረኛ ምርት ውድድሩን ማከናወን ትልቅ ነገር እንደሆነ ገልፀዋል። ጥቅምት 4 ተጠባቂው የሩጫ ውድድር የሚደረግ ሲሆን በማግስቱ ጥቅምት 5 ደግሞ ታላላቅ እንግዶች የሚሳተፉበት \”ኢምፓክት አዋርድ\” በዲሲ ከተማ እንደሚደረግ አመላክተው ከጎፈሬ ጋር ባደረጉት ስምምነት ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል።
መድረኩን በቀጣይነት የተረከቡት አቶ ሳሙኤል ተቋማቸው ጎፈሬ በእግርኳሱ በደንብ ብራንዱን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ አንስተው በቀጣይ በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ መስራት ለሚያስቡት ሥራ ትልቅ በር እንደሚከፍት ተናግረዋል። ጨምረውም ምርታቸውን በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ተደራሽ እያደረጉ ቢገኙም በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገራት ያለውን የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ፍላጎት ለመመለስም መንገድ ከፋች ስምምነት እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጧል።
ከ4 ሺ በላይ ተሳታፊዎች በሚኖሩት ውድድር ላይ ጎፈሬ ሙሉ የመወዳደሪያ ትጥቆችን እና የአስተባባሪዎች ልብሶችን የማጓጓዧ ወጪዎችን ሸፍኖ በስፖንሰር መልክ የሚያቀርብ ይሆናል። በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ ተቋማት ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት አብረው ለመስራት ቢፈራረሙም የአፈፃፀም ሂደት ታይቶ ውሉ ለተጨማሪ ዓመታት እንደሚታደስ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሰንዝረው ምላሽ ከተሰጠ በኋላ የፎቶ መነሳት መርሐ-ግብር ተከናውኖ መግለጫው ተገባዷል።