ወላይታ ድቻ የታዳጊ ቡድኑ ፍሬ የሆኑትን ሁለት ተጫዋቾች ውላቸውን ማራዘሙን ክለቡ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል።
ለቀጣዩ የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን ዋና አሰልጣኛቸው አድርገው የሾሙት ወላይታ ድቻዎች ራሳቸውን ለማጠናከር አዳዲስ ተጫዋቾችን ከማስፈረማቸው በፊት በክለቡ ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ውል ማራዘምን ቀዳሚው ተግባራቸው አድርገዋል። በዚህም መሠረት ከክለቡ የታችኛው ቡድን ፍሬ የሆኑትን ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ እና ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለን ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት በክለቡ እንደሚቆዩ ውላቸው መታደሱን ስራ አስኪያጁ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ ያለፉትን አምስት ዓመታት በዋናው ቡድን ውስጥ በግብ ጠባቂነት ያገለገለው ቢኒያም ገነቱ እና በተመሳሳይ ከክለቡ ከ20 ዓመት በታች ቡድን የተገኘው እና በሶዶ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ተጫውቶ በድጋሚ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ወደ ልጅነት ክለቡ ተመልሶ ሲያገለግል የቆየው ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ በቡድኑ ውስጥ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት መቆየታቸው ዕርግጥ ሆኗል።