ሀዋሳ ከተማ የስድስት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

ከቀናት በፊት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ኮንትራት ያራዘሙት ሀዋሳ ከተማዎች በዛሬው ዕለት የስድስት ተጫዋቾችን ውል አድሰዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀጣይ ዓመት ተሳትፎውን የተሻለ ለማድረግ ከአዳዲስ ተጫዋቾች ዝውውር በፊት የነባር ተጫዋቾችን ውል ማራዘም የጀመረው የሀዋሳ ከተማ የስድስት ተጫዋቾችን ኮንትራትን ለተጨማሪ ዓመት ማራዘሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል።
\"\"
ዓሊ ሱለይማን ውሉን ካራዘሙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ኤርትራዊው የመስመር እና የፊት አጥቂ ስፍራ ተሰላፊው በሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት በመፈረም ውሉን ያደሰው የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ሁለተኛው ውሉን ያደሰው አማካዩ አብዱልባሲጥ ከማል ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ ተጫዋች ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በክለቡ ለመቆየት ውሉን አራዝሟል። ሦስተኛው ውሉን ያራዘመው ተጫዋች አቤኔዘር ኦቴ ነው። የቀድሞው የኢኮስኮ ፣ ደቡብ ፓሊስ ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ስልጤ ወራቤ የግራ መስመር ተከላካይ በሀዋሳ ተጨማሪ ዓመትን ለማሳለፍ ውል ካደሱት መሐል ተጠቅሷል።

\"\"

የክለቡ የታዳጊ ቡድን ፍሬ የሆነው እና ከዚህ ቀደም በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተብሎ የተሸለመው አጥቂው ምንተስኖት እንድሪያስ ፣ በተመሳሳይ ከወጣት ቡድኑ የተገኙት የመሐል ተከላካዩ ፀጋአብ ዮሐንስ እና አማካዩ አቤኔዘር ዮሐንስ በክለቡ ውል በዛሬው ዕለት ያራዘሙ ሌሎቹ ተጫዋቾች ሆነዋል።
\"\"