በዝውውር መስኮቱ እስካሁን ተሳትፎ ያላደረገው ድሬዳዋ ከተማ የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል።
በአሠልጣኝ አስራት አባተ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በዚህ ሳምንት ወደ ዝውውር ገበያው እየገቡ ሲሆን አዳዲስ ተጫዋቾችን ከማናገር ጎን ለጎን የነባር ተጫዋቾችን ውል ማራዘም ጀምረዋል። በዚህም ከደቂቃዎች በፊት የሁለት ተጫዋቾችን ውል ማራዘማቸው ታውቋል።
ውሉን ለተጨማሪ ዓመት ያራዘመው የመጀመሪያው ተጫዋች ሱራፌል ጌታቸው ነው። የቀድሞ የአዳማ ከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋች ያለፉትን ሁለት ዓመታት በቆየበት ድሬዳዋ ቤት ለመቀጠል ውሉን አራዝሟል።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ አጥቂው ቻርለስ ሙሴጌ ነው። ዩጋንዳዊው አጥቂ በዓመቱ መጀመሪያ ባህር ዳር ላይ በተከናወነው የጣና ካፕ ውድድር ለሞደርን ጋዳፊ ሲጫወት የነበረ ሲሆን ወዲያው በድሬዎች ዐይን ገብቶ ፊርማውን አኑሮ የኢትዮጵያን እግርኳስ መተዋወቁ አይዘነጋም። አሁንም በክለቡ ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል።