የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-2 ሙገር ሲሚንቶ – ታክቲካዊ ትንታኔ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር-ሊግ 3ኛ ሳምንት

እሁድ ጥቅምት 30 2007 ዓ.ም 11፡00 – አዲስ አባባ ስታዲየም

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-2 ሙገር ሲሚንቶ

ታክቲካዊ ትንታኔ – በሚልክያስ አበራ

 

ፀኃዩ በረድ ሲል አመሻሹ አካባቢ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀድሞ ከተካሄደው ግጥሚያ በተሻለ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ገና በመጀመሪያዎቹ 5 ደቂቃዎች ውስጥ እንድንመለከት አስችሎናል፡፡ የሙገሩ ግብ ጠባቂ በንግድ ባንክ አጥቂዎች የተደረጉበትን አደገኛ ሙከራዎች በጥሩ ብቃት ማዳን መቻሉ ቡድኑ በመጨረሻ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አግዞታል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4-1-4-1 (በጨዋታው ሂደት ከአጥቂዎቹ ጀርባ የነበሩት ሁለቱ የመሃል ሜዳ አማካዮች ሁለገብነት (versatility) ፎረሜሽኑን በመከላከል ቅርፅ 4-3-3 ሲያስመስለው ታይቷል፡፡)

ሙገር ሲሚንቶ ደግሞ 4-4-2/4-4-1-1 ፎርሜሽንን ተጠቅመዋል፡፡ (ምስል1)

Bank 2-2 Mugher (1)

የመጀመሪያው 45 የባንክ የበላይነት

ንግድ ባንኮች ጨዋታውን በ4-1-4-1 ቢጀምሩትም በሂደት የቡድናቸው ቅርጽ ተደጋጋሚ ለውጥን ሲያሳይ ነበር፡፡ በእርግጥ ፎርሜሽኑ በጨዋታ እንቅስቃሴ ከ4-2-3-1 ወይም ከ4-3-3 ሊመጣ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ አጨዋወቱ ማጥቃትንም ይሁን መከላከልን ሚዛናዊ በሆነ የተጫዋቾች ቁጥር ለማካሄድ ስለሚያስችል በሁለቱም phases (Defending and Attacking) ሚዛናዊነትን ያስጠብቃል፡፡ 4-1-4-1 ተጫዋቾች በ 4-2-3-1 እና በ 4-3-3 ላይ የሚያገኙትን የመሀል ሜዳ የጎነ ሶስት ማእዘናት ለማስገኘት ያስችላል፡፡

4-2-3-1ን የሚጠቀም ቡድን ከሁለቱ የመሀል የተከላካይ አማካዮች አንደኛውን ወደ ፊት በማስጠጋት ወይም ከ 4-3-3 ፎርሜሽን ደግሞ ከመሀል 2ቱን የማጥቃት አማካዮች ከሁለቱ wide forwards በመቀላቀል እና አጥቂውን የበለጠ ወደ ፊት ተጠግቶ ለቡድኑ የ Depth ጥቅም እንዲያስገኝ በማድረግ 4-1-4-1 ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከፎርሜሽኑ የሚነገሩ ጠቀሜታዎች አንዱና ዋነኛው tactical flexibilityን ( የታክቲክ መዋለልን ) የሚፈቅድ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በማጥቃትም ይሁን በመከላከል ፈጣን transition (ሽግግር)ን ማስገኘት ይችላል፡፡ በተጨማሪም ከአማካይ ተከላካዩ ፊትለፊት የሚጫወቱት ሁለት የአጥቂ አማካዮች ከኋላቸው ማለትም ከ አማካይ ተከላካዩ በቀኝና በግራ (በጎነዮሽ) ያሉትን ቦታዎች በሁለገብነት ሚና እንዲጫወቱበት ያደርጋቸዋል፡፡ ይህንንም የንግድ ባንኮቹ 8 (ሰለሞን ገ/መድህን) እና 10 (አብዱልከሪም ሃሰን) በአግባቡ ሲጠቀሙበት ተስተውሏል፡፡

በንግድ ባንክ የመሃል ሜዳ የአማካይ ተከላካይነት ሚና 18 ቁጥሩ (አምበሉ ታዲዮስ ወልዴ) ቦታውን በአግባቡ ለመሸፈን ከፊቱ ካሉ አማካዮች ጋር የነበረው መግባባት እና ሚዛናዊ የመከላከል እና የማጥቃት ተሳትፎ እጅግ መልካም ነበር፡፡ አምበልነቱንም በአግባቡ ሲወጣ ነበር፡፡ ተከላካዮቹም High-line በመስራት (ወደ መሃል ሜዳው ተጠግተው) በመከላከል የነበራቸው ድርሻ ጥሩ ነበር፡፡ ፉልባኮቹም ቢሆኑ በተለይ በቀኝ መስመር የተሰለፈው15 ቁጥሩ (አዲሱ ካሳ) ግዜውን የጠበቀ overlapping ለመጀመርያው የፊሊፕ ዳውዚ ጎል ወሳኝ ነበረች፡፡

የመስመር ሚዛናዊነትን በተመለከተም በአንዱ መስመር ያለው ፉልባክ ሲያጠቃ በሌላኛው ወገን ያለው ደግሞ ሲከላከሉ ታይቷል፡፡

የሙገሮች 4-4-2

ሙገሮች የተለመደውን 4-4-2 ሲጠቀሙ ነው ያመሹት፡፡ በጨዋታ ሒደት ከመከላክል ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረ ቢሆኑም በተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ላይ የነበራቸው የተጫዋቾች ቁጥር አናሳነት እጅጉን ሲጎዳቸው ተስተውሏል፡፡ ተከላካዮቻቸው ወደ ራሳቸው የጎል ከልል ቀርበው መከላከላቸው እና የተከላካይ አማካዮቻቸውም በመስመሮች መካከል ያለውን ቦታ ለማጥበብ የደረጉት ጥረት እጥቂዎቻቸውን የበለጠ ተነጥለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ ወደ ኋላ ያፈገፈገው 4-4-2 ለንግድ ባንኮች ጥልቀት (Depth) እንዲሁም ስፋት (Width)ን እንዲጠቀሙ ረድቷቸዋል፡፡ የመስመር አማካዮቻቸውም ቢሆኑ የበለጠ የመከላከል ተግባር ላይ ግዜ ሲያጠፉ ታይተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል በ 31ኛው ደቂቃ አከባቢ ሙገሮች ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሽግግር ሲያደርጉ የንግድ ባነኮች 8 ተጫዋቾች በራሳቸው የሜዳ ክፍል መገኘታቸው ምን ያህል ሙገሮች ዘገምተኛ ሽግግር ( translition) ሲያደርጉ እንደነበር አመላካች ነው፡፡

በተጨማሪም ንግድ ባንኮች የሙገሮችን ጠንካራ መስመር ሲከላከሉ ደካማውን ደግሞ ሲያጠቁ መታየታቸው ተጨማሪ ጎል ሲያስገኝላቸው እነደሚችል ያመላክት ነበር፡፡ የሙገሩ የግራ መስመር ተከላካይ (13 ቁጥሩ) በተደጋጋሚ ያለ ሽፋን ቦታውን ለቆ ሲወጣ ይታይ ነበር፡፡

በ36ኛው ደቂቃ ላይም በዚህ መስመር ጥሩ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው የባንኩ አዲሱ ካሳ (የቀኝ መስመር ተከላካይ) ከፊቱ ካለው አማካይ (8 ቁጥሩ) ጋር በመሆን ባንድ ሁለት ቅብብል ሰንጥቀው በመግባት ፉልባኩ ያስቆጠረው ጎል ቡድኑን በቀላሉ የ 2 ለ 0 መሪነት አጎናጽፎታል፡፡

የአሰልጣኝ ግርማ ኃ/ዮሃንስ የሰመረ የታከቲክ ለውጥ

በወጣት ልጆች ላይ በመስራት የሚታወቁት እና ለረጅም ግዜ ክለቡን በአሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ግርማ ኃ/ዮሃንስ የአጨዋወት ስልት አና የታክቲክ አተገባበር እነዲሁም የተጫዋቾች ሚና በሚያስገርም መልኩ በመቀየር ውጤታቸውን ከ2-0 ወደ 2-2 መለወጥ ችለዋል፡፡ የጨዋታውን መልክ በመቀየራቸውም ሊደነቁ ይገባል፡፡

አሰልጣኙ ቡድኑ ከእረፍት በፊት ንግድ ባንክ ሲጠቀምበት የዋለውን የግራ መስመራቸውን ፉልባክ ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት በመቀየርና በግራ መስመር ደግሞ በመከላከል የተሻለ የነበረውን የቀኝ መስመር ተከላካይ በማጫወት የንግድ ባነኩን የቀኝ ፉልባክ የማጥቃት ሚና መግታት ችለዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ሙሉ ተከላካዮቻቸውን ወደ መሃለኛው የሜዳ ክልል ተጠግተው እንዲጫወቱ በማዘዝ ተጋጣሚያቸውን press ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ይህም በነጻነት ሲጫወቱ የነበሩትን የባንክ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የመቀባበያ አማራጮችን በመድፈን እና Attacking angles ን በማጥበብ የተሳካ የመከላከል ስራ ሰርተዋል፡፡ ከዕረፍት በፊት ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያልታየውን የቀኝ መስመር አማካዩን( 21 ቁጥር) በመተካትና የቀኝ መስመሩን የአማካይነት ሚና ለ 18 ቁጥር በመስጠት (ወደ ኃላ ተስቦ) እንዲጫወት በማድረግ የባንክ ተከላካዮች ላይ ጫና ፈጥለው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡

የግራ መስመር አማካይ ላይም የተጫዋች ለውጥ አድርገው (21ን አስወጥተው ፈጣኑን እና ብዙ የሜዳ ክፍል የሚያዳርሰውን 12 አስገበተዋል፡፡) በዚህም የቀኝ መስመር የበላይነትን ለማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በ72ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር 12 ቁጥሩ መስርቶ የሄደውን ጥሩ ኳስ 10 ቁጥሩ ጌድዮን አካፖ ጎል አድርጓታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኙ ቀይረው ያስገቧቸው ተጫዋቾች ቴክኒካዊ ችሎታቸው እና ታከቲካዊ ግንዛቤያቸው የተሻለ እንደነበር የሚያሳዩ ብዙ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ በተለይ የሙገሩ 12 ቁጥር በአጥቂዎቹና በአማካዮቹ መካከል link ለመፍጠር ያደረገው ጥረት በ 92ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶለታል-ለ10 ቁጥሩ ጎል መቆጠር ምክንያት የሆነች ኳስን ለ7 ቁጥሩ አመቻችቶ በማቀበል፡፡ አጥቂውም በመሃል ተከላካዮች መሃል የነበረችውን መጠነኛ ክፍተት ተጠቅሞ ጎሏን ሊያስቆጥር ችሏል፡፡ ባንኮች በመጨረሻ አከባቢ የአጥቂ ተጫዋች እና አማካይ የግራ መስመር ለውጥ ለማድረግ ቢሞክሩም የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡

ምስል2

Bank 2-2 Mugher (2)

 

ያጋሩ