የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉው ሀዋሳ ከተማ አመሻሹን የሁለት አዳዲስ ተጫዋቾች ዝውውር ሲያጠናቅቅ የአንድ ተጫዋች ውል ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ክፍተት አለብኝ ባላቸው ቦታዎች ላይ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ እንየው ካሳሁንን ወደ ስብስቡ አስቀድሞ የቀላቀለ ሲሆን የስድስት ነባሮችንም ውል ቀደም ብሎ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ክለቡ አመሻሹን ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ ደግሞ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአንድ ተጫዋች ውልም አራዝሟል።
ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ሁለተኛው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል። በአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስን ከጀመረ በኋላ በመቀጠል በባህርዳር ከተማ እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በወላይታ ድቻ ተጫውቶ አሳልፎ በክለብ ህይወቱ አራተኛ መዳረሻውን ወደ ኃይቆቹ አድርጓል።
የተከላካይ አማካዩ አማኑኤል ጎበና ሌላኛው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ መሆኑም ተረጋግጧል። በአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ የጀመረው እና በመቀጠል በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ፣ ሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ከ2014 ጀምሮ በአዳማ ሲጫወት ከቆየ በኋላ ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቷል።
ሀዋሳ ከተማ ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ በክለቡ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታትን ማሳለፍ የቻለውን የቀድሞው የደደቢት ፣ ወልዋሎ እና ሀድያ ሆሳዕና የመስመር ተከላካይ የሆነውን መድሀኔ ብርሀኔን ውሉን ለሁለት ተጨማሪ ዓመት አራዝሞለታል።