በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ሁለቱ ክለቦች ዝግጅታቸውን ነገ ይጀምራሉ

በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን በቻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚወክሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ በነገው ዕለት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ።

የ2023 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከሦስት ሳምንታት በኋላ መደረግ ይጀምራሉ። በዚህ ሁለት አህጉራዊ ውድድሮች ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ላይ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሻምፒዮንስ ሊጉ ተከታዩ ባህርዳር ከተማ በበኩሉ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ላይ የሚካፈሉ ሲሆን በተመሳሳይ ሁለቱም ክለቦች በነገው ዕለት ሰኞ ሐምሌ 24 ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል።
\"\"
የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሱት ፈረሰኞቹ በነገው ዕለት ቢሾፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ማረፊያቸውን አድርገው በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እየተመሩ ዝግጅታቸውን ማከናወን ይጀምራሉ። ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም ጋር በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚጠብቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች እስከ አሁን አማኑኤል አረቦን በዝውውሩ ወደ ክለባቸው በመቀላቀል የአስር ነባር ተጫዋቾችን ውልም ያደሱ ሲሆን ከሰሞኑ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር በማጠናቀቅ ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾች ውልም እንደሚያራዝሙ ይጠበቃል።
\"\"
ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትለው በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው በማጠናቀቃቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፉት ባህርዳር ከተማዎች ለውድድሩ ቀደም ብለው ወደ ዝውውሩ በመግባት ፍሬው ሰለሞን ፣ አላዛር ማርቆስ ፣ ረጀብ ሚፍታህ ፣ ፍሬዘር ካሳ እና አይቮሪያኑን ተከላካይ አብዱላዚዝ ሲያሆኔን ያስፈረሙ ሲሆን የሁለት ተጫዋቾችን ውልም ማራዘማቸው ይታወሳል። ከታንዛኒያው አዛም ጋር በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ያለባቸው የጣና ሞገዶቹ በነገው ዕለት በክለቡ መቀመጫ ከተማ ባህርዳር አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመያዝ በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው መሪነት ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ።