በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወሳኝ ጨዋታዎች ከፊቱ ያሉበት ባህር ዳር ከተማ ማሊያዊ አጥቂ ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።
በአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ የ2015 የሊጉን ውድድር በሁለተኝነት ካገባደደ በኋላ ለአፍሪካ ኮንፈዴሬሽን ካፕ እና ለቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ዝግጅቱን በዛሬው ዕለት በዓፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ጀምሯል። ክለቡ ቡድኑን በአዳዲስ ተጫዋቾች እያጠናከረ የሚገኝ ሲሆን መጠነኛ ክፍተት በነበረበት የፊት መስመር ቦታም ተጫዋች ለማስፈረም መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች።
ክለቡን በአንድ ዓመት ውል ለመቀላቀል ስምምነት የፈፀመው ተጫዋች ሱሌይማን ትራኦሬ ነው። በማሊ ባማኮ የተወለደው አጥቂው የሀገሩን ክለብ ጨምሮ በሞሮኮ፣ ቡልጋሪያ፣ ዲ አር ኮንጎ እና ሴኔጋል ክለቦች ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሽ የኢትዮጵያን እግርኳስ በመተዋወቅ በለገጣፎ ለገዳዲ ቆይታ እንዳደረገ አይዘነጋም። እንደገለፅነው ተጫዋቹ ከባህር ዳር ጋር ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን በቅርቡም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ቡድኑን በይፋ ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።