በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎን እያደረገ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት ላይ ደርሷል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከስድስት ዓመታት በኋላ በቀጣዩ ዓመት መሳተፍ የሚጀምረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላቅ ባለ መልኩ አዳዲስ ተጫዋቾችን የክለቡ አካል ያደረገ ሲሆን ጋናዊውን ካሌብ አማንኩዋን የግሉ ማድረጉ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ የውጪ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለማምጣት ቅድመ ስምምነት መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።
አማካዩ ባሲሩ ዑመር ወደ ክለቡ ለማምራት የተስማማው የመጀመሪያ ተጫዋች ነው። በሀገሩ ጋና ክለቦች አሻንቲ ኮቶኮ ፣ ዋፋ እና ካሬላ ዩናይትድ ተጫውቶ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ መድን ያሳለፈው ተጫዋቹ ንግድ ባንክን ለመቀላቀል ተስማምቷል።
ሌላኛው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ለመሆን የተስማማው ዩጋንዳዊው ተጫዋች ሲሞን ፒተር ነው። በአጥቂ እና በአማካይ ስፍራ ላይ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ ባህርዳር ላይ ተካሂዶ ከነበረው አማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይለሀገሩ ክለብ ቡል ሲጫወት ከታየ በኋላ በኢትዮጵያ መድን ቆይታን አድርጎ ቀጣዩ መዳረጋቸው ንግድ ባንክ ሊሆን በእጅጉ ተቃርቧል።
ሁለቱም ተጫዋቾች ከቀደመው ክለባቸው ኢትዮጵያ መድን ጋር እስከ መስከረም ወር ድረስ ውል ያላቸው ቢሆንም በቀጣዩ ዓመት በንግድ ባንክ እንደምንመለከታቸው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።