ቢጫዎቹ ተስፈ የጣሉበትን ተጫዋች በቡድናቸው ለማቆየት ተስማሙ

ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ የመጀመርያ ፕሮፌሽናል ኮንትራት ተፈራረመ።

በማካቢ ቴል አቪቭ ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው ተስፈኞች የሚጠቀሰው የአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የመስመር ተጫዋች ኦረል ባየ በእግር ኳስ ሂወቱ የመጀመርያው ፕሮፌሽናል ውል ተፈራረመ። እስከ 2026 ድረስ ከእናት ክለቡ ማካቢ ቴል አቪቭ ለመቆየት ከተስማማ በኋላም በእስራኤል ዋናው ሊግ ተሳታፊ ለሆነው ሀፓይል ሀደራ በውሰት ተሰጥቷል።
\"\"
በቡድኑ የአስራ ዘጠኝ ዓመት ቡድን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየት ባለፈው የውድድር ዓመት ከማካቢ ጃፋ ጋር በተደረገው የስቴት ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ ለዋናው ቡድን የተሰለፈው ይህ ተስፈኛ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለታዳጊ ቡድኑ አስራ ዘጠኝ ጨዋታዎች አካሂዶ ስምንት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ከቁጥሩ ባሻገር ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳሳየ የሚነገርለት ይህ ተጫዋች በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።

\"\"

ተጫዋቹ ከስምምነቱ በኋላ በሰጠው ሀሳብም \” በአስራ ሦስት ዓመቴ ይህንን ቡድን ስቀላቀል ለዋናው ቡድን የመጫወት ትልቅ ህልም ነበረኝ፤ ዛሬ ደግሞ ህልሜን አሳክቻለው\” ብሏል። የክለቡ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ ቤን ማንስፎርድ ደግሞ ክለባቸው ትልቅ ተስፋ የሚጥልበትን ተጫዋች በክለቡ ማቆየቱ ደስታ እንደፈጠረላቸው በመግለፅ የተጫዋቹ ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ ገልፀዋል።
\"\"
ውሉን በተፈራረመበት ማግስት ለተጫማሪ ልምድ በውሰት ያመራው ይህ ወጣት ተጫዋች ከዚህ ቀደም ለእስራኤል ከአስራ ዘጠኝ ዓመት ብሄራዊ ቡድን ሰባት ጨዋታዎች አካሂዶ አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል።