የሊጉ ተወዳዳሪ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ከተማ በያዝነው ሳምንት ዝግጅቱን ይጀምራል።
ሰርቪያዊውን አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪችን የክለቡ አለቃ በማድረግ የሾመው የመዲናይቱ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ለቀጣዩ የውድድር ዘመን በዝውውር መስኮቱ እስከ አሁን አስራት ሚሻሞን በብቸኝነት የክለቡ አዲስ አካል ያደረገ ሲሆን በቀጣይም ከሀገር ውጪ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ይጠበቃል። አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪችን በአካል ብቃት አሰልጣኝነት አብረዋቸው እንዲሰሩ የሀገራቸው ሰው የሆኑትን ማርኮ ቫስሊሴቪጅን ያመጡ ሲሆን ክለቡን በአዳማ ከተማ በያዝነው ሳምንት ዝግጅቱን ይጀምራል።
የክለቡ አካላት ወደ አዳማ የፊታችን ሐሙስ ካመሩ በኋላ ዕለተ ዕርብ ነሀሴ 5 በይፋ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ። እንደ ክለቡ ገለፃ ከሆነ ዓመቱን በጉዳት የቋጨው ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጀ ወደ ሜዳ ሲመለስ በአንፃሩ ሮቤል ተክለሚካኤል ፣ አስራት ቶንጆ እና መሐመድ ኑር ናስር በጉዳት እንደማይኖሩ ተመላክቷል።