ከመስከረም 13 ጀምሮ በሀዋሳ ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ክልል ካስቴል ዋንጫ በዛሬው እለት በሀዋሳ ከተማ ስታድየም ሲጠናቀቅ አርባምንጭ ከተማ ሲዳማ ቡናን በመርታት የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡
አስቀድሞ 07:00 ላይ ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ፋሲል ከተማ ከ ወላይታ ድቻ የመደበኛውን ክፍለ ጊዜ ያለግብ አጠናቀው በተሰጡ የመለያ ምቶች ፋሲል 5-4 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡
ግማሽ ቡድኑን ከጣና ሀይቅ የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰብያ ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ ወደ ባህርዳር የላከው ፋሲል 2 ተጫዋቾች ብቻ ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጦ ለመጫወት ተገዷል፡፡ ሆኖም ጨዋታውን በማቀዝቀዝና ወደ መለያ ምት ለማምራት በሚመስል እንቅስቃሴ ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አካሂደው በመጨሻም በመለያ ምቶች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ቀጥሎ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ስታድየሙን በሞላ ደጋፊ ታጅቦ ተካሂዶ በአርባምንጭ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ፈጣን እንቅሰቃሴ በነበረው የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ከግራ መስመር አብዱለጢፍ መሐመድን በመጠቀም አደገኛ የማጥቃት እንቅስቀሴ ቢያደርጉም ተጠቃሽ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም፡፡ ጨዋታው ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ መጥቶ በቀጣዮቹ 15 ደቂቃ ምንም የግብ ሙከራ ያልተደረገበት እና የተቆራረጡ ቅብብሎች የታዩበት ሆኗል፡፡
በ36ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ ከቀኝ መስመር አምልጦ በመውጣት ሳጥኑ ሲገባ በአርባምንጭ ተከላካዮች የተሰራበችን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ መትቶ በግቡ ቋሚ ወደ ውጪ ሰዷታል፡፡ ከ3 ደቂቃዎች በኋላ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ምንተስኖት አበራ ሞክሮ አቅጣጫውን ሲስት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ላኪ ሳኒ ከሳጥኑ የቀኝ መስመር አቅጣጫ አክርሮ በመምታት በቀድሞ ክለቡ ላይ አስቆጥሮ አርባምንጭ ከተማን መሪ በማድረግ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
በተጫዋቾች ጉዳት በተደጋጋሚ ሲቆራረጥ በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ በአርባምንጭ የሜዳ ክፍል ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የጠራ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተመስገን ካስትሮ እና አንድነት አዳነ የተመራው የአርባምንጭ የተከላካይ መስመርም የሲዳማን ማጥቃት በአግባቡ ተቆጣጥሮ ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተካሄደው የሽልማት ስነስርአት የሚከተሉት ተጫዋቾች ፣ ዳኞች እና ክለቦች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ኮከብ ተጫዋች – ተካልኝ ደጀኔ (አርባምንጭ)
ኮከብ አሰልጣኝ – ጸጋዬ ኪዳነማርያም (አርባምንጭ)
ኮከብ ግብ ጠባቂ – ፍቅሩ ወዴሳ (ሲዳማ ቡና)
ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች – ዮናታን ከበደ ፣ ፊሊፕ ዳውዝ እና ጃኮ አራፋት (3 ጎሎች)
ምስጉን ዳኞች – ዋና ዳኛ ማኑሄ ገብረጻድቅ ፣ ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ
የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ – ሲዳማ ቡና
3ኛ ደረጃ – ፋሲል ከተማ
2ኛ ደረጃ – ሲዳማ ቡና
1ኛ ደረጃ – አርባምንጭ ከተማ