በ2007 ድሬዳዋ ላይ በተካሄደው የብሔራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን በመቀላቀል በ2008 የውድድር ዓመት ወደ ሊጉ በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ሀዲያ ሆሳዕና በ2009 በጳውሎስ ጌታቸው እየተመራ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ ከጫፍ ደርሶ በመለያ ጨዋታ ተሸንፎ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ክለቡ በ2010 የውድድር ዓመት ከአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሮ የተለያዩ ለውጦችን በማድረግ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት የጳውሎስ ጌታቸው ረዳት አሰልጣኝ የነበረው እዮብ ማለን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሲሾም በ2009 ድሬዳዋ ላይ በተካሄደው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ደሴ ከተማን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማሳደግ የቻለው ዮሴፍ ያለውን ምክትል አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡ በተጨማሪም አዲስ ቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር መቀመጫውን ሆሳዕና አድርጎ ከመስከረም ወር መጀመርያ አንስቶ በአቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም በቀን 2 ጊዜ ልምምድ በመስራት ቅድመ ዝግጅቱን ጀምሯል::
ሀዲያ ሆሳዕና በአመቱ ጉዞው ላይ ወሳኝ ሚና ሲወጡ የነበሩ 7 ተጫዋቾቹን ሲያጣ ከአምናው ስብስብ ከ8 በላይ ተጫዋቾችን አቆይቷል፡፡ 16 አዳዲስ ተጫዋቾችን ደግሞ ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡
የፈረሙት ተጫዋቾች ዝርዝር
ግብ ጠቂዎች
ፍሬው ገረመው(ደቡብ ፖሊስ)፣ ማቲዎስ ሰለሞን (ነቀምት ከተማ)
ተከላካዮች
ዳኛቸው በቀለ (አዲስ አበባ ፖሊስ)፣ አብነት አባተ (ወሎ ኮምቦልቻ)፣ ሐብታሙ ለገሰ (ወሎ ኮምቦልቻ)፣ አሸብር ታከለ (መተሃራ ስኳር)፣ ፍሬው ኪዳኔ (ሀላባ ከተማ)፣ ጅላሉ ከድር (ሱሉልታ ከተማ)
አማካዮች
ማቲያስ መኮንን (ደሴ ከተማ)፣ መሐመድ ከድር (ስልጤ ወራቤ)፣ ሙሉቀን ተስፋዬ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)፣ ሙሉቀን ወልዴ (ወሎ ኮምቦልቻ)፣ አብዱልለጢፍ ሙራድ (አራዳ ክ/ከተማ)
አጥቂዎች
ኢብሳ በፍቃዱ(ነቀምት ከተማ)፣ ተዘራ አቡቴ (ጅማ ከተማ)፣ መለሰ ትዕዛዙ (አማራ ውሃ ስራ)
ሀዲያ ሆሳዕና በ 2010 የውድድር ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የክለቡን አወቃቀር እና አደረጃጀት ላይ ለውጥ በማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ፕሪምየር ሊጉን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ ያላሳካውን ዘንድሮ ለማሳካት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ እዮብ ማለ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ” ሀዲያ ሆሳዕና በ2009 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ክለቡ ባሳየው ፉክክር ኩራት ይሰማናል፡፡ በክለቡ የሚታየውን የተጫዋቾች ስነ ምግባር በማስተካከል እና በውድድር አመቱ የነበረብንን ድክመት በመቅረፍ በቡድኑ ላይ የአንድነት ስሜት በመፍጠር ደጋፊው የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ እኔ ዘንድሮ የምገነባው ቡድን ሙሉ በሙሉ ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ይሆናል፡፡ ተጫዋቾቼን በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና በማዘጋጀትም በደጋፊዎቻችን ታግዘን ፕሪምየር ሊጉን እንደምንቀላቀል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ” ሲሉ የቀድሞው የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ኮከብ ገልጸዋል፡፡
ሀዲያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ለ የተደለደለ ሲሆን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን ጥቅምት 25 ከስልጤ ወራቤ ጋር በሜዳው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰብያ ስታድየም የሚያከናውን ይሆናል፡፡
በከፍተኛ ሊጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል በክረምቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ እና ያለፈው አመት ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ዘንድሮ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ክለቦችን ዝግጅት በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን፡፡