​አአ ከተማ ዋንጫ| ኢትዮጵያ ቡና ሌላኛው የፍፃሜ ተፋላሚ ሆኗል

12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ሁለተኛ ቀን መርሃ ግብር ዛሬ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ቡና መስኡድ መሀመድ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በመታገዝ ለእሁዱ የፍፃሜ ጨዋታ አልፏል፡፡

በመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ግብ በተደጋጋሚ መድረስ ቢችሉም የተገኙትን እድሎች ግን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በተለይም በሁለተኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚና እያሱ ታምሩ በተከታታይ ወደ ግብ ሞክረው የኤሌክትሪክ ተከላካዮችና ግብጠባቂው ተረባርበው አድነዋል፡፡ በተመሳሳይ በሶስተኛው ደቂቃ ቶማስ ስምረቱ ከማእዘን የተሻማለትን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ሳይጠቀምባት የቀረችው ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡

ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በርካታ ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ውጤታማ አልነበሩም፡፡


እምብዛም ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ከሚመቱና ኢላማቸውን ካልጠበቁ ሙከራዎች በቀር የረባ የጠሩ የግብ ሙከራ አጋጣሚዎች ባልታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በተለይም ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ እንዲሁም የተከላካይ አማካዩ ኄኖክ ካሳሁን አደገኛ በሆኑ ቀጠናዎች ላይ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን በተደጋጋሚ ኳሶችን በኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ቢነጠቁም የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች እነዚህን ኳሶች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው በተሻለ በመልሶ ማጥቃት የኢትዮጵያ ቡናን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ መፈተን ችለዋል፡፡ በመሀል ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ በሚቆራረጡ የኳስ ቅብብሎች እንዲሁም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የሀይል አጨዋወትና በተጫዋቾች መካከል የነበሩ ጉሽሚያዎች በሁለተኛው አጋማሽ ሁሉ በርከት ብለው ተስተውለዋል፡፡


በ73ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ ከግራ መስመር ያሳለፈለትን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ መሀል ካጠበበ በኃላ ያቀበለውን ኳስ አስቻለው ግርማ ሞክሮ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ያደረጓት ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡ ከዚች ሙከራ በአንድ ደቂቃ ልዮነት በ74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አስራት ቱንጆ በመስመሮች መካከል ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ አሻግሮ መስኡድ በጥሩ ሁኔታ ኳሷን ከመረብ በማዋሀድ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና የ1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው እሁድ በ10 ሰአት ለ12ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ የሚፉለሙ ይሆናል፡፡


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኢትዮጵያ ቡናው አምበል መስኡድ መሀመድ የጨዋታ ኮከብ በመባል የተዘጋጀለትን ሽልማት ተረክቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *