የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ክለብ የሆነው ቲፒ ማዜምቤ ለሁለተኛ ተከታታይ ግዜ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ፍፃሜ መድረስ ያቻለበትን ውጤት በሞሮኮ መዲና ራባት ላይ አስመዝግቧል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በሜዳው ንጊታ ማንላንጎ ግብ 1-0 ማሸፍ የቻለው የሉቡምባሺው ክለብ ከፉስ ራባት ጋር ያለግብ አቻ በመለያየቱ ነው ለፍፃሜ መድረስ የቻለው፡፡
በኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ሞላይ አል ሃሰን በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳው ፉስ ራባት ጠንካራውን የማዜምቤን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ በጨዋታውም በርካታ የግብ ሙከራዎችን ሳናይበት አልፏል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ የታየበት መሆኑን ተከትሎ የመልሱ ጨዋታ ቢጠበቅም ከመጀመሪያው ጨዋታ ባነሰ መልኩ ፉክክር ተስተናግዶባታል፡፡
ቲፒ ማዜምቤ ያለፉትን ሶስት ዓመታት በተከታታይ ካፍ በሚያዘጋጃቸውን የክለቦች ውድድር ለፍፃሜ በመቅረብ ጠንካራነቱን አሳይቷል፡፡ ማዜምቤ በ2015 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግን ዩኤስኤም አልጀርን በመርታት ሲያሸንፍ አምና በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ሌላኛው የአልጄሪያ ክለብ ሞውሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ ዳግም በኮንፌድሬሽን ዋንጫው ለፍፃሜ መድረስ ችሏል፡፡
የቀድሞ የካታንጋ ግዛት ገዢ እና የቲፒ ማዜምቤ ባለቤት ሞይስ ካቱምቢ ከዲ.ሪ. ኮንጎ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ለረጅም ዘመናት ሃገሪቱን እየመሩ ከሚገኙት እና ስልጣንን ከአባታቸው ሎረን ካቢላ ከተረከቡት ጆሴፍ ካቢላ ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ኑሯቸውን በሎንደን ማድረጋቸውን ተከትሎ ለክለቡ የሚያደርጉት ድጋፍ ቢቀዛቀዝም የክለቡ አካዳሚ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾችን ማውጣት መጀመሩ ማዜምቤን በአፍሪካ ውድድሮች ላይ አሁንም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎታል፡፡
ዛሬ ቱኒዝ ላይ ክለብ አፍሪካ የደቡብ አፍሪካውን ሱፐርስፖርት ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት ፕሪቶሪያ ላይ 1-1 መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
የቅዳሜ ውጤት
ፋት ዩኒየን ስፖርት 0-0 ቲፒ ማዜምቤ (0-1)
የእሁድ ጨዋታ
3፡00 – ክለብ አፍሪካ ከ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (1-1) (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)