(ማቲያስ ኃይለማርያም ከመቐለ)
የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከ2 ሳምንት ‘ሙከራ’ መቐለ ከተማን ለመረከብ መወሰናቸው ታውቋል፡፡ ክለቡ 3 አዳዲስ ተጫዋቾችንም አስፈርሟል፡፡
መቐለ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ከኃላፊነት ካነሳ በኋላ ዮሀንስን ሳህሌን ለመቅጠር ቢያስብም አሰልጣኙ በቅድሚያ የቡድኑን ሁኔታ ተመልክተው እንደሚወስኑ መግለጻቸውን ተከትሎ እስካሁን ሳይፈርሙ ቆይተዋል፡፡ ክለቡ በነገው እለትም የአሰልጣኙን ቅጥር በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ያሰለጠኑት ዮሀንስ ከደደቢት በመቀጠል ሁለተኛ የፕሪምየር ሊግ ክለብ የሚያሰለጥኑ ይሆናል፡፡
መቐለ ከተማ የተጫዋቾች ዝውውር ላይ አሁንም ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ሳምንትም 3 ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል፡፡ ጋናዊው የመስመር ተከላካይ አቼምፖንግ አሞስ እና ሌላው ጋናዊ አጥቂ ቢስማርክ ኦቦሜንግ መፈረማቸውን ተከትሎም ክለቡ በስብስቡ የያዛቸውን የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር 5 አድርሷል፡፡ ፍቃዱ ደነቀ ሌላው ለክለቡ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ በመሀል ተከላካይ እና በመስመረ ርተከላካይነት መሰለፍ የሚችለው ፍቃዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መፍረስ ተከትሎ ወደ መቐለ አምርቷል፡፡
መቐለ በርካታ ተጫዋቾችን እያስፈረመ እንደመሆኑ ከስብስቡ ተጫዋቾችን በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡ በክረምቱ ከወሎ ኮምቦልቻ ክለቡን የተቀላቀለው ግብ ጠባቂው ሙሴ ዮሀንስ ወደ ሽረ እንዳስላሴ በውሰት ሲያመራ ክብሮም አስመላሽ እና ሐድሸ አወጣኸኝ የተቀነሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡