የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ኬኖያን ተክቶ በቻን ውድድር ላይ እንዲካፈል ከካፍ የቀረበለትን ግብዣ ባለመቀበሉ ኢትዮዽያ እና ሩዋንዳ በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ አላፊው እንዲታወቅ መወሰኑ ይታወሳል።
የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ጠዋት ደብዳቤ ለካፍ መላኩ የተሰማ ሲሆን የደብዳቤው ፍሬ ሀሳብ ይህንን ጨዋታ ለማድረግ የተሰጠን ጊዜ አጭር በመሆኑ ጨዋታው እንዲራዘምልን እንጠይቃለን የሚል እንደሆነ ታውቋል። ታዲያ አሁን እየተጠበቀ ያለው የካፍ ምላሽ ብቻ ሲሆን ምንአልባት ካፍ በምላሹ ጨዋታው በወጣለት ቀን መደረግ አለበት ብሎ ካሳወቀ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታው ራሱን ሊያገል እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል። አሁን ባለው ሁኔታ የቻን የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ህዳር ወር እንዲወጣ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ስለዚህ ከጊዜ እጥረት አንፃር ካፍ የኢትዮጵያን ጥያቄ የመቀበል እድሉ ጠባብ ነው፡፡
ፌዴሬሽኑ የዝግጅት ጊዜ በቂ አይደለም ቢልም ከውስጥ አዋቂዎች እንደሰማነው ከሆነ የበጀት እጥረት እና በጨዋታው ሽንፈት የሚመጣ ከሆነ ከጫና ለመራቅ ታስቦ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። አስገራሚው ነገር ግን የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ለመዘጋጀት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረኩ ነው ለማለት በሚመስል መልኩ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለ25 ተጨዋቾች ጥሪ አድርገዋል። ዛሬ ካፒታል ሆቴል እንደሚሰባሰቡ ቢነገርም ሳይሰባሰቡ ቀርቷል። አሁን እየሰማነው እንደሆነ መረጃ ከሆነ ደግሞ ጥሪውን ተቀብለው የተወሰኑ ተጫዋቾች ቢመጡም ጥሪ እንዳልተደረገላቸው ተነግሯቸው ተመልሰዋል ።
ብሔራዊ ቡድኑ ምስቅልቅል ውስጥ ሆኖ የመሳተፍ አለመሳተፉን ጉዳይ ነገ ቁርጡ እንደሚለይለት ይጠበቃል፡፡