ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን ከሜዳቸውን ውጪ 2-0 በማሸነፍ ምድብ አራትን በመሪነት አጠናቃ ወደ ዓለም ዋንጫው ማምሯትን አረጋግጣለች፡፡
ጋናዊው የመሃል ዳኛ ጆሴፍ ላምፕቲ በጨዋታ ውጤት ማስቀየር እና ማጭበርበር ላይ ተሳትፏዋል በሚል ይህ ጨዋታ በድጋሚ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በሜዳዋ ፖልክዋኔ ላይ በሴኔጋል 2-0 ተሸንፋ ከዓለም ዋንጫው ውጪ ሆናለች፡፡ ይህ ምድብ አራቱም ሃገራት የማለፍ እድል የነበራቸው ቢሆንም በስተመጨረሻ ሴኔጋል አንድ ጨዋታ እየቀራት ከ2002 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ዓለም ዋንጫው ተመልሳለች፡፡ የሴኔጋልን የድል ግቦች ዲያፍራ ሳኮ እና የባፋና ባፋናው ቶማሳንካ ምኪዝ በራሱ ግብ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥረዋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዳካር ላይ የሚገናኙ ይሆናል፡፡
የሴኔጋሉ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ በ2002 ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በጣምራ ባስተናገዱት የዓለም ዋንጫ ከዚህ ዓለም በካንሰር ህመም ምክንያት በሞት በተለየው ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ብሩኖ ሜትሱ መሪነት እስከሩብ ፍፃሜ መጓዝ የቻለው የሴኔጋል ቡድን ውስጥ አምበል ነበር፡፡ ሲሴ አሁን ደግሞ በአሰልጣኝነት ሴኔጋልን ወደ ዓለም ዋንጫው መልሷል፡፡ ሴኔጋል እንደ ሳድዮ ማኔ፣ ኬይታ ባልዴ ዲያኦ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ቼክ ኮያቴ እና ሙሳ ሶ የመሳሰሉ ኮከዋክብትን ይዞ ወደ ሩሲያው የ2018 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች፡፡
በምድብ ሁለት ለክብር እና መርሃ ግብር ማሟያነት በዘለለ የደረጃ ለውጥ ባማያስከትለው ጨዋታ ኮንስታንታይን ላይ አልጄሪያ በአዲሱ አሰልጣኝ ራባህ ማጀር እየተመራች ከናይጄሪያ ጋር 1-1 ተለያይታለች፡፡ ናይጄሪያ አስቀድማ ወደ ዓለም ዋንጫ ማምሯቷ ይታወቃል፡፡ ጆን ኦጉ ናይጄሪያን ቀዳሚ ሲያደርግ ያሲን ብራሂሚ በፍፁም ቅጣት ምት በ88ኛው ደቂቃ አልጄሪያን አቻ አድርጓል፡፡ ናይጄሪያ በምድብ ጨዋታዎች ሳትሸነፍ የበላይ ሆኗ ስታጠናቅቅ በአንፃሩ ደግሞ አልጄሪያ አንድም ጨዋታ ሳታሸንፍ የምድቡ ግርጌ ላይ ለመቀመጠ ተገዳለች፡፡
እስካሁን ሶስት ተሳታፊ ሃገራት ከአፍሪካ ዞን ታውቀዋል፡፡ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ግብፅ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገራት ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት ቦታዎች ከቱኒዚያ ወይም ዲ.ሪ. ኮንጎ ከምድብ አንድ እንዲሁም ሞሮኮ ወይም ኮትዲቯር ከምድብ ሶስት እንደሚያልፉ ይጠበቃል፡፡ የሰሜን አፍሪካዊቹ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ ያለባቸውን ጨዋታዎችን በድል ከተወጡ ወይም አቻ ውጤት ማግኘት ከቻሉ ወደ ዓለም ዋንጫው ሲያመሩ ኮትዲቯር ሞሮኮን ማሸነፍ ብቻ ወደ ዓለም ዋንጫው ይመልሳታል፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ የጠበበ እድል የያዘች ይመስላል፡፡ ኮንጎ ጊኒን ኪንሻሳ ላይ አሸንፋ የቱኒዚያን በሊቢያ መሸነፍ መጠበቅ የግድ ይላታል፡፡
የአርብ ውጤቶች
ደቡብ አፍሪካ 0-2 ሴኔጋል
አልጄሪያ 1-1 ናይጄሪያ
የቅዳሜ ጨዋታዎች
10፡00 – ዛምቢያ ከ ካሜሮን (ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም)
11፡30 – ጋቦን ከ ማሊ (ስታደ ፍራንስቪል)
2፡30 – ዲ.ሪ. ኮንጎ ከ ጊኒ (ኮምፕሌክስ ኦምኒ ስፖርትስ ስታደ ደስ ማርቲርስ)
2፡30 – ቱኒዚያ ከ ሊቢያ (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)
2፡30 – ኮትዲቯር ከ ሞሮኮ (ስታደ ፊሊክስ ሆፖት ቦይግኒ)
የእሁድ ጨዋታዎች
11፡30 – ኮንጎ ሪፐብሊክ ከ ዩጋንዳ (ስታደ አልፎንሶ ማሳምባ ዴባት)
12፡30 – ጋና ከ ግብፅ (ኬፕ ኮስት ስታዲየም)