በ2ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደርቢነት መንፈስ ከሚንፀባረቁባቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የሲዳማ ቡና እና አርባምነጭ ከተማ ጨዋታ ይርጋለም ላይ ተካሂዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ሲዳማ ቡና የመጀመሪያውን ሳምንት ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሳይጫወት ሲቀር በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማ 2ኛውን ጨዋታ ያከናወነው አርባምንጭ በመቀለው ጨዋታ ከተጠቀመው ስብስብ አማካዩን አለልኝ አዘነን በዮናታን ከበደ ብቻ በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በበርካታ ደጋፊዎች የታጀበውና አልፎ አልፎ ያልተገቡ አጨዋወቶች የተስተዋሉበት ይህ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን የተስተናገደበት ቢሆንም በተደጋጋሚ በዳኛ ፊሽካ እንቅስቃሴዎች መቆራረጣቸው ጨዋታውን እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ሲዳማ ቡናዎች ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት አደጋ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡
ወንድሜነህ ዘሪሁን የአበበ ጥላሁንና የማይክል አናንን ስህተት ተጠቅሞ ግልፅ የማግባት አጋጣሚን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ምናልባትም አርባምንጭን መሪ ማድረግ የሚችልበት መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ በ20ኛው ደቂቃ ተካልኝ ደጀኔ በግራ በኩል ያሻገራትን ኳስ አበበ ጥላሁን ለግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በግንባሩ ለመስጠት ሲሞክር ኳሷ በማጠሯ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ናይጄሪያዊው አጥቂ ላኪ ሰኒ በቀድሞው ክለቡ ላይ አስቆጥሮ አርባምንጭ ከተማን ቀዳሚ አድርጎል፡፡
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሲዳማ ቡናዎች በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን 25ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ ግብ ሞክሮ ሲሳይ ባንጫ ሲመልስበት ዳግም የተመለሰውን ኳስ አብዱለጢፍ መሀመድ በቀጥታ መትቶ በእለቱ ድንቅ የነበረው ሲሳይ ባንጫ አድኖበታል፡፡
ከ40ኛው ደቂቃ በኃላ ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነ ብርሀን የወሰኗቸው ውሳኔዎች አወዛጋቢ ነበሩ፡፡ በተለይ 43ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረው ኳስ ላኪ ሰኒ ከተከላካዮች ጀርባ በመገኘት ወደ ግብ ሲያመራ የሲዳማው ተከላካይ ግሩም አሰፋ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ከኃላ ጠልፎ በመጣሉ ግልፅ የግብ እድልን አባክኖብናል ፣ የቅጣት ምት ሊሰጠንና በቀይ ካርድ ሊወጣ ይገባ ነበር በማለት አርባምንጭ ከተማዎች ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ክስ ለማስመዝገብ ጨዋታው ለ7 ደቂቃን ባክኖ ቢጀመርም የመጀመሪያው አጋማሽ በአዞወቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ተጨማሪ አጥቂ ወደ ሜዳ በማስገባት የአቻነት ግብ ለማግኘት የሞከሩ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በጥብቅ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ ተስተውሏል፡፡ ባለሜዳወቹ በአዲስ ግደይ እና ባዬ ገዛኸኝ አማካኝነት ጥሩ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይ ባዬ በ67ኛው ደቂቃ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሐብታሙ ገዛኸኝ ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች፡፡ በአርባምንጮች በኩል ወንድሜነህ ዘሪሁን ከአለልኝ አዘነ የተሻገረችውን የቅጣት ምት ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ሲመታ አግዳሚው የመለሰበት ሙከራ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ የምታደርግ አጋጣሚ ነበረች፡፡
70ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች የመሀለኛው ሜዳ የግራ ክፍል ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ፍፁም ተፈሪ ሲያሻማ በአርባምንጭ የግብ ክልል ውስጥ እንዳለ ከበደ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል፡፡
ከአቻነቷ ግብ በኃላ ሲዳማ ቡናዎች የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ ፍፁም የበላይ ቢሆኑም የአርባምንጭ ከተማ የተከላካይ መስመርን መስበር ሳይችሉ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና
“ጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀስንበት ቢሆንም ተጋጣሚያችን የሚሰሩት ያልተገቡ አጨዋወቶች እና አስደሳች ያልሆነ እንቅስቃሴ ያሰብነውን እንዳናደርግ አድርጎናል፡፡ እግርኳሳችን ወዴት እየሄደ እንደሆነ የተመለከትንበት ነበር፡፡ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ኳስ እንዲባክን በሆነ ባልሆነው እየወደቁ ሰአት የሚያባክኑበት ሁኔታን ተመልክተናል፡፡ እኛ ግን በሚገባ ኳሱን ተቆጣጥረን ተጫውተናል፡፡ እነሱ አስቀድመው የሰራነውን ስህተት ተጠቅመው አስቆጥረውብናል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ስህተቶቻችን ታርመን ከተጋጣሚያችን በልጠን መጫወት ብንችልም ብዙ ማግባት የምንችላቸውን እድሎችንም መጠቀም አልቻልንም፡፡ በቀጣይ ጨዋታ ከሜዳችን ውጭ ከወልዋሎ አለን ያን ለማሸነፍ በቀጣይ እንዘጋጃለን፡፡
ፀጋዬ ኪዳነማርያም – አርባምንጭ ከተማ
” ውጤቱ ለሁለታችንም የሚያስከፋ አይመስለኝም፡፡በርካታ ጎል ማስቆጠር የምንችልባቸው አጋጣሚዎችም ተፈጥረው ነበር፡፡ በጣም ከባድ እና በአሰልጣኝነት ዘመኔ ተመልክቼ የማላውቀው እልህ አስጨራሽ ጨዋታን አይቼበታለው፡፡ በደሎች ቢደርሱብንም ተቋቁመን መውጣት ችለናል፡፡ በእግርኳስ መከላከል እና ማጥቃት ያለ ባህሪ ነው፡፡ የመጨረሻ ደቂቃዎችላይ እነሱ የተሻሉ ስለነበሩም ነው ለመከላከል የተገደድነው፡፡
” ለምን ትክክለኛ ውሳኔ እንደማይሰጥ ግራ አጋብቶኛል፡፡ በዳኝነቱ ግልፅ የሆኑ በደሎች ደርሰውብናል፡፡ በጨዋታው ስሜታዊ ሆኜ ልናገር ያስገደደኝም የታዩት ያልተገቡ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ አላስፈላጊ ካርዶችና ጫናዎች ተደርጎብናል፡፡”