ሴካፋ
የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን 22 ተጫዋቾችን በመያዝ የሴካፋ ዋንጫ ዝግጅቱን በይፋ ጀምሯል። በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጥሪ ቀርቦላቸው ያልተገኙት ተስፋዬ አለባቸው እና ብሩክ ቀልቦሬ ( ወልዲያ ) ፣ ዮናስ ገረመው እና ኄኖክ አዱኛ ( ጅማ አባጅፋር) እንዲሁም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ( መቐለ ከተማ ) ዛሬ ማምሻውን ካፒታል ሆቴል በመገኘት ሪፖርት ያደረጉ በመሆኑ ከነገ ጀምሮ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ዝግጅት የሚጀምሩ ይሆናል።
በተያያዘ ዜና ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚገኙት 27ቱ ተጨዋቾች በአራተኛ ሳምንት በሚኖረው የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ ወደ ክለባቸው በመሄድ ተጫውተው እንደሚመለሱ ሰምተናል።
ኢርያ
የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ አቅራቢ የሆነው የጣልያኑ ኩባንያ ኢሪያ ለብሔራዊ ቡድኑ አስቀድሞ ካስገባቸው የተሻለ እና የጥራት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ትጥቆች በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ሰምተናል። አስቀድመው በገቡ የብሔራዊ ቡድኑ ትጥቆች የጥራት ደረጃ ላይ ጥያቄ ይነሳ የነበረ ሲሆን አሁን የምርቱ ስራ ተጠናቆ ወደ አአ የሚመጣው ትጥቅ የተሻለ እንደሆነ ታውቋል።
ኢርያ በኢትዮዽያ ወኪል ድርጅት ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ ሲገኝ ከብሔራዊ ቡድኑ ባሻገር ለደደቢት እግርኳስ ክለብ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል። በቀጣይ ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር ተጨማሪ ስምምነት ይፈፅማል ተብሏል።
የክልል እጩዎች
እስከ ህዳር 15 ድረስ ክልሎች በቀጣዩ አራት አመት የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በበላይነት የሚመሩ እጩዎች እየቀረቡ ባሉበት በአሁኑ ሰአት የትግራይ ክልል ኮሎኔል አወል አብዱራሂም እና ወ/ገብርኤል መዝገቡ የስራ አስፈፃሚ ተወካይ በመሆን እንደተመረጠ ሲረጋገጥ የኦሮምያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፕሬዝደንት እና በስራ አስፈፃሚነት አስቀድመው የተወከሉት እጩ ግለሰቦችን በሌላ እጩ እንደተቀየሩ ከፌዴሬሽኑ ይፋዊ ማረጋገጫ ባይሰጥም ዜናው በስፋት እየተነገ ይገኛል። ሌሎች ክልሎች የእጩ አቶተወካዮቻቸውን ብዛት እና ስም ዝርዝር በነገው እለት አልያም የመጨረሻ ቀን እስከተባለው አርብ ድረስ አጠቃለው ያቀርባሉ ተብሏል ።
ጠቅላላ ጉባዔ
ጥቅምት 30 እና ህዳር 1 ቀን በተካሔደው እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አስመራጭ ኮሚቴ መመረጥ ሲገባው ለአላስፈላጊ ወጪ እና የጊዜ ብክነት አስከትሎ ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ነገ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ሆኗል ።
የኢትዮዽያነገ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔታል አዲስ ሆቴል በሚካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በዋናነት የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ ፣ የእጩ ተወካዮች ብዛት በዋናነት የጉባኤው አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የፊፋ አልያም የካፍ ተወካይ በጉባኤው ላይ ስለመገኘታቸው እስካሁን ከፌዴሬሽኑ ማረጋገጫ አላገኘንም።
ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን
በሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ድሬዳዋ ላይ ሊካሄድ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና መከላከያ በአንደኛ ዲቪዚዮን ድሬደዋ ከተማ ላይ ሊካሄድ የነበረው የ3ኛ ሳምንት ጨዋታ እንደማይካሄድ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ይህንን ተከትሎም በ3ኛ ሳምንት የሚደረጉት ሁሉም ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል።
በሌላ ዜና የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር መቋረጡ ቅር እንዳሰኛቸው አንዳንድ ቡድኖች ተናገሩ። “ውድድሩ በመቋረጡ ተጫዋቾችን እረፍት ሰጥተን እንደገና ለውድድር ማዘጋጀት ከባድ ነው። በቀጣይ በቡድናችን ጉዞ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል” ብለዋል ።
አክሊሉ አየነው
ከፋሲል ከተማ ጋር በዝውውር ምክንያት ውዝግብ ውስጥ በመግባቱ ያለፉትን ወራት በየትኛውም ጨዋታ ላይ ሳንመለከተው የቆየነው አክሊሉ አየነው ጉዳይ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ በማግኘቱ እና የመጫወት ፍቃድ ቲሴራ ያገኘ ሲሆን ነገ ከኢትዮዽያ ቡና ከሲዳማ ቡና ጋር በሚኖረው ጨዋታ ላይ በመጀመርያ አሰላለፍ አልያም በተቀያሪ ወንበር ልንመለከተው እንደምንችል ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያሳያል ።
የወጣቶች እግርኳስ
ከ17 እና ከ20 አመት በታች ተሳታፊ ቡድኖች ተለይተው ታወቁ። በ2009 ለመጀመርያ ጊዜ በተጀመረው ከ20 አመት በታች የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 12 ቡድኖች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በዘንድሮ አመት የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር 15 ደርሷል። አምና ከነበሩት መካከል ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ በመፍረሱ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ ሲሆን ሲዳማ ቡና ፣ አአ ከተማ ፣ ጥሩነሽ ዲባባ ስ/አካዳሚ እና አሰላ ጭላሎ ፏዱ ኮፕሌክስ በአዲስ መልክ ውድድሩን የተቀላቀሉ ቡድኖች ናቸው ።
ከ17 አመት በታች አምና ከነበሩት 15 ቡድኖች ሐረር ሲቲ እና ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ከውድድሩ ሲወጡ ሲዳማ ቡና እና ዱከም ከተማ በአዲስ መልክ ውድድሩ ላይ የሚቀላቀሉ ሆኖ በአጠቃላይ 14 ቡድኖች ተሳታፊ ይሆናሉ ።
የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን
ባሳለፍነው እሁድ በጀመረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን አንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲካሄድ ምንትዋብ ዮሐንስ ባስቆጠረችው ብቸኛ ጎል ኢትዮዽያ ቡና ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲን 1-0 አሸንፏል። ሊጉ በቀጣዩ ሳምንት በወጣለት መርሀ ግብር መሰረት በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ የሚቀጥል ይሆናል ።