ዳንኤል አጄይ ወደ ሀገሩ አምርቷል
በዘንድሮ የውድድር አመት ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀለው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄይ በግል ጉዳይ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀገሩ ያቀና ሲሆን ክለቡ ጅማ አባ ጅፋር በአራተኛ ሳምንት መቐለ ላይ ከመቐለ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ያልተሰለፈ መሆኑ የሚታወቅ ነው። እስካሁን ከሄደበት በመመለስ ከክለቡ ጋር ያልተቀላቀለ መሆኑ ሲታወቅ በቀሩት ሁለት ቀናት እንደሚመለስ እና ከሲዳማ ቡና ጋር ላለው ጨዋታ ሊደርስ እንደሚችል ሶከር ኢትዮዽያ ማረጋገጫ ያገኘች ቢሆንም አሁን እየሰማነው የሚገኘው መረጃ ሀገሩ ሳይሆን ሆላንድ እንደሚገኝ እየተሰማ መሆኑ ምን አልባት የመመለሱን ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል።
የክለቦች ጥያቄ
በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ደንብን አስመልክቶ ከሰሞኑን በሚደረጉ የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ክለቦች በአንድ ጨዋታ ላይ አንድ ክለብ በመጀመርያ 11 አሰላለፍ ውስጥ ምንያህል የውጭ ተጨዋቾችን መጠቀም ይችላል በሚል ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል። በሁለተኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ላይ ሲዳማ ቡና በአንድ ጨዋታ 4 የውጭ ተጨዋቾችን ሲጠቀም ድሬዳዋ ከተማ ከ ደደቢት በተካሄደው ጨዋታ ድሬደዋ ከተማ በተመሳሳይ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አራት የውጭ ተጨዋቾችን መጠቀሙን ተከትሎ ደደቢቶች ይህን ጥያቄ ማንሳታቸው ይታወሳል። የክለቦች የተጨዋቾችን ተገቢነት አስመልክቶ እያነሱ ያሉትን ጥያቄ ይዘን ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ እያቀረብን ሲሆን ፌዴሬሽኑም በቅርብ ቀን ለክለቦች ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ አሳውቆናል ።
ሲዳማ ቡና
በአራተኛ ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ትላንት በሜዳውና በደጋፊው ፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1- 0 የተረታው ሲዳማ ቡና ለብሔራዊ ቡድን አገልግሎት ያመሩት አበበ ጣላሁን እና አዲስ ግደይ እስከጨዋታው መቃረቢያ ድረስ ወደ ለጨዋታው እንደሚደርሱ ከብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ማረጋገጫ ቢደርሳቸውም ለጨዋታው አለመድረሳቸው ቅሬታ እንደተሰማቸውና በቡድኑ ውጤት ማጣት አንዱ ምክንያት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ማጣት እንደሆነ ገልፀዋል ።
ከ17 እና ከ20 አመት በታች
የ2010 የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ከ17 እና ከ20 አመት በታች ውድድር እስካሁን ያልጀመረ ሲሆን ለመዘግየቱ እንደ ምክንያት እየቀረበ ያለው ጉዳይ የታዳጊዎቹን የእድሜ ተገቢነት የMRI ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደነበረ እና አሁን ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ይፋ ባይሆንም ታህሳስ 3 የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት እንደሚደረግ ሰምተናል።
ዝውውር
አሁን ባለው የቡድናቸው ጉዞ እና ውጤት ደስተኛ ያልሆኑ ቡድኖች ገና ከወዲሁ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሳይከፈት በቡድናቸው ውስጥ አለ ባሉበት ክፍተት ላይ ተጨዋቾችን በማምጣት ቡድኑን ለማጠናከር ይረዳቸው ዘንድ ከሀገር ውስጥም ከውጭ ሀገራት ተጨዋቾችን በማስመጣት በሙከራ ጊዜ አይተው አላየልይም በቀጥታ ለማስፈረም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ታውቋል።
የፌዴሬሽን ምርጫ
ታህሳስ 16 በአፋር ከተማ ሰመራ ለሚካሄደው የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ባለፈው ሳምንት በሁለት ኮሚቴ የተከፈለ 13 አባላት ያሉበት አስመራጭ ኮሚቴ መመረጡ ይታወቃል። አስመራጭ ኮሚቴውም የመጀመርያ ስብሳባውን የዕጩ ተመራጮችን ስም ከፌዴሬሽን በመረከብ ስራቸውን ጀምረዋል። በቀረቡት 30 እጩ ተመራጮች ዙርያ የተገቢነት ምርመራ ከቅዳሜ ጀምሮ በመሰብሰብ ስራቸውን የሚሰሩ ሲሆን አጠቃላይ የደረሱበትን ደረጃ በይፋ በቅርቡ ሁሉም የሚዲያ አካላት በተከኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ሰምተናል።
ኢንተርናሽናል ዳኞች
በ2018 በፊፋ እና ካፍ የሚደረጉ ውድድሮችና በዋና ዳኝነትና በረዳት ዳኝነት የሚመሩ ዳኞችን ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ የቲዮሪ እና የአካል ብቃት ፈተና መስጠቱ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ከሰሞኑ ፊፋ ለየሀገራቱ የዳኞቹን ማረጋገጫ ባጅ የላከ ሲሆን ኢትዮዽያም የኢንተርናሽናል ዳኞች ባጅ ከተላከላት ሀገር አንዷ ናት። በወንዶች ሁለት አዲስ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ (ቴዎድሮስ ምትኩ እና ዳዊት አሳምነው) ስታገኝ ዘካርያስ ግርማ እና ሀይለየሱሱ ባዘዘው የኢንተርናሽናል ባጁን ያጡ ናቸው። በሴቶችም በተመሳሳይ ሁለት አዲስ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች ፀሀይነሽ አበበ እና አስናቀች ገብሬ ሲሆኑ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጃቸውን ያጡት ፅጌ ሲሳይ እና ፍቅረገነት አሳምኔ ናቸው። በሴት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት አዜብ አየለ እና ይልፋሸዋ አበበ አዲስ ረዳት ዳኛ ሆነው ሲመረጡ ማህሌት አስራት እና ብርቱካን ማሞ የኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት ባጃቸው ያጡ ናቸው። ከዚህ ውጭ አስቀድመው የነበሩ ኢንተርናሽናል ዳኞች መሆናቸው ታውቋል ።
ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሴቶች
ሁለተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከእሁድ አንስቶ በተካሄዱ ጨዋታዎች ቀጥሎ ተካሂዷል።
ሻሸመኔ ከተማ 1-0 ቂርቆስ ክ/ከተማ
ቦሌ ክ/ከተማ 3-3 ቅ/ማርያም ዩኒቨርስቲ
አቃቂ ክ/ከተማ 2-4 ጥሩነሽ ዲባባ
ንፋስ ስልክ ከ ከ ልደታ ክ/ከተማ (ሐሙስ በ09:00)
አአ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ (ሀሙስ በ11:00)
ወጣቶች አካዳሚ ከ ጥረት ኮርፓሬት (አርብ 09:00)
*ጎንደር ላይ መካሄድ የነበረበት የፋሲል ከተማ እና የኢትዮዽያ ቡና ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል።
የደጋፊዎች የፓናል ስብሰባ
የፊታችን እሁድ አዲግራት ከተማ ላይ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት እና ኢትዮዽያ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ አስመልክቶ የወልዋሎ ስፖርት ሀላፊዎች እና የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር በጋራ በመሆን ከጨዋታው አንድ ቀን አስቀድሞ ቅዳሜ ከሰአት ጀምሮ የደጋፊዎች ፓናል ስብሰባ እንደሚካሄድ የሰማን ሲሆን በውይይቱም ጠቃሚ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።
አንደኛ ሊግ
የኢትዮዽያ 1ኛ ሊግ ህዳር 24 ይጀመራል ቢባልም ክለቦች በበቂ ሁኔታ ክፍያቸውን ባለማጠናቀቃቸው ምክንያት ለአንድ ሳምንት ሊራዘም እንደሚችል ተነግሯል።
ዮርዳኖስ አባይ
ዘንድሮ ጫማውን እንደሰቀለ የተነገረው የቀድሞው የኤሌክትሪክ ኮከብ ዮርዳኖስ አባይ ከአድናቂዎቹ ጋር በክብር ለመለያየት በማሰብ የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሰማን ሲሆን የዝግጅቱ አንዱ አካል የሆነው የእግርኳስ ህይወት ዘመኑን የሚገልፅ ዘጋቢ ፊልም እያዘጋጀ እንደሆነ እና በቅርቡ እንደተጠናቀቀ ለህዝቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ናትናኤል ዘለቀ
ከታዳጊ ቡድን አንስቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በብሔራዊ ቡድን ድረስ እየተጫወተ የሚገኘው የአማካኝ ተከላካዩ ናትናኤል ዘለቀ ጀርባው ላይ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ለተሻለ ህክምና ዛሬ ወደ ህንድ አምርቷል። ህመሙ ሳይታወቅ በውስጡ እንደቆየ የተነገረው የናትናኤል ጉዳት በክለቡ ሙሉ ወጪ በህንድ በሚኖረው የ21 ቀን ቆይታ ከፍተኛ የህክምና ክትትል በማድረግ ከጤናው አገግሞ እንደሚመለስ ሰምተናል። ከዚህ ቀደም አሉላ ግርማ አዲስ ፈራሚው ታደለ መንገሻ ወደ ህንድ አምርተው የተሳካ የህክምና ቆይታ አድርገው መመለሳቸው ይታወቃል።
መስማት የተሳናት እንስት ተጫዋች
ያለፉትን 14 አመት በተከላካይና በአማካይ ስፋራ ለአለቤ ሾው ፣ ለአዳማ ከተማ ፣ ለድሬዳዋ ከተማ ተጫውታለች። ድንቅ ተጨዋች እንደሆነች የሚነገርላት ብፅአት ፋሲል ይህን ሁሉ አመት እግርኳስን ስትጫወት አስገራሚ የሚያደርጋት መስማት የተሳናት መሆኗ ነው። ብዙ ነገሮችን በሚጠይቀው የእግርኳስ ጨዋታ መስማት አለመቻሏ ሳይገድባት ይሄን ያህል አመት በምልክት እና እግርኳሳዊ ቋንቋ እየተጠቀመች መዝለቋ አስገራሚ ያደርጋታል። ከዚች እንስት ተጫዋች ጋር ሶከር ኢትዮዽያ ስለ ህይወት ውጣ ውረዷ አስመልክቶ በቅርብ ቀን በቃለ ምልልስ እንደምንመጣ ከወዲሁ እናሳውቃለን ።
የፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት እውነታዎች
አራተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ሁለም ጨዋታዎች በአአ እና በክልል ከተማዎች ተካሂዶ ትላንት ተጠናቋል። በስምንት ጨዋታዎች 9 ጎል ሲቆጠር በአንድ ጨዋታ ብዙ ጎል የተቆጠረበት በወልዋሎ አዲግራት ኢትዮ ኤሌትሪክ 3-1 ባሸነፈበት ጨዋታ የተመዘገበ ውጤት ነው። ሁለቱ ደግሞ በራስ ግብ ላይ የተቆጠሩ ናቸው። 23 ቢጫ እና 2 ቀይ ካርዶች በስምንት ጨዋታ ተመዝግበዋል። እንዳአምናው ሁሉ ዘንድሮም ሊጉ የጎል ድርቅ እየመታው ሲገኝ አሁንም አሳሳቢው ጉዳይ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ነው።