በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻሉን ቀጥሎበታል።
አርባምንጮች ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ከነበረው ጨዋታ የሶስት ተጨዋቾች ቅያሪ ሲያደርጉ ከሴካፋ የተመለሱት እንዳለ ከበደ እና ተመስገን ካስትሮ እንዲሁም ወንደሰን ሚልኪያስ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ገብተዋል። አቡበከር ሳኒን እና አበባው ቡጣቆን ከብሔራዊ ቡድን ምርጫ መልስ ያገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስም ለጋዲሳ መብራቴ እና አዳነ ግርማም የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል በመስጠት ከሸገር ደርቢው ቡድን ውስጥ የአራት ተጨዋች ለውጥ አድርጓል።
የመጀመሪያው አጋማሽ በፍጥነቱ ዝግ ያለ እና ሙከራ አልባ ሆኖ ነበር ያለፈው። የቅዱስ ጊዮርጊስን አማካዮች ሰው በሰው በመያዝ እንደልባቸው ኳስ እንዳይቀባበሉ በማድረጉ ረገድ ተሳክቶላቸው የነበሩት አርባምንጮች በማጥቃቱ በኩል እጅግ ደካማ ነበሩ። የፊት አጥቂው ላኪ ሳኒ እና ከጀርባው የነበሩት ሶስት አማካዮች ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ላይ በተጋጣሚው ሜዳ ሲገኝ የነበራቸው ቦታ አያያዝ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ለመከላከል ከባድ አልነበረም። ይህ በመሆኑም አዞዎቹ ያገኟቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በአግባቡ ወደ ግብ አጋጣሚነት ሲቀይሩ አልተስተዋሉም። በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል የነበረው እንቅስቃሴም ከሙከራዎች የተቆጠበ ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ በኩል የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ቅብብላቸው ወደ ሶስቱ የፊት አጥቂዎቻቸው እንደልብ ሲደርስ አልታየም። በተጋጣሚ ሰው በሰው የተያዙት አማካዮቻቸውን ለመርዳት አልፎ አልፎ ብቻ ወደ መሀል ሲሳቡ የነበሩት የመስመር አጥቂዎች በሚፈጥሩት ክፍተት በተለይ በቀኝ መስመር ያደላ የማጥቃት እንቅስቃሴን ሲያደርጉ ቢታዩም በአርባምንጭ ሳጥን ውስጥ ለመግባት የቻሉት በጥቂት አጋጣሚዎች ነበር። ያም ቢሆን ግን የመጀመሪያው አጋማሽ ከማብቃቱ በፊት መሪ መሆን አልተቸገሩም። ጎሏ 43ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተገኘውን ኳስ አዳነ እና ኒኪማ በመቀባባል ወደ አርባ ምንጭ ሳጥን ከተጠጉ በኃላ ኒኪማ ለፎፋና አሳልፎለት ፎፍና በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ ኳስ ለማስጣል ሸርተቴ የገባውን ተካልኝ ደጀኔን ጨርፋ በአንተነህ መሳ መረብ ላይ ያረፈች ነበረች።
በሁለተኛውም አጋማሽ በተመሳሳይ መልኩ ኳስ ይዞ ለመጫወት የሚሞክር ቅዱስ ጊዮርጊስን እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን በመጠባበቅ በራሱ አጋማሽ ላይ ቆይቶ የሚከላከልን አርባምንጭን አሳይቶናል። እንግዶቹ አርባምንጮች በቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ በገቡባቸው አጋጣሚዎች በቁጥር እየተበለጡ ወደ ሮበርት ከመቅረባቸው በፊት ኳሶቻቸው በቀላሉ ሲበላሹ ተስተውሏል። ላኪ ሳኒን ቀይሮ የገባው ብርሀኑ አዳሙ 61ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር አስቻለውን አልፎ ሰብሮ ከገባ በኃላ ወደ ውስጥ ያሳለፈው እና ማንም ሳይደርበት የቀረው ኳስ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ብርሀኑ ሞክሮት ሮበርት በቀላሉ ካዳነበት ሙከራ ውጪ አርባምንጮች በጨዋታው ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ አልተመለከትንም። በርካታ የቆሙ ኳሶችን ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በእንቅስቃሴም ሆነ ከቆሙ ኳሶቹ መነሻነት የፈጠሯቸው ዕድሎች ከነበራቸው የጨዋታ ብልጫ አንፃር አጥጋቢ የሚባል አልነበረም። 69ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ካነሳው የማዕዘን ምት ፎፋና በግንባሩ ሞክሮ ወደውጪ ከወጣበት በኃላ ቡድኑ ሌላ ሙከራ ሳያደርግ ቢቆይም በመጨረሻ ግን ሁለት ግቦችን አክሎ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም አርባምንጭን 3-0 ማሸነፍ አልተሳነውም። ግቦቹም 83ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ያስቆጠረውና በጭማሪ ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር አሻምቶት አንተነህ ማውጣት ሳይችል ቀርቶ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ያስቆጠሯቸው ነበሩ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን አስራአንድ በማድረስ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አርባምንጭ ከሽንፈት በኃላ ከዘጠነኛ ወደ አስራሁለተኛ ደረጃ ተንሸራቷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
“ጨዋታው ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። በተለይም ጎል እስክናገኝ ድረስ። ተጋጣሚያችን ወደ ጎሉ በጣም ተስቦ ይከላከል ስለነበር የምንፈልጋቸውን ያህል የጎል ዕድሎች አልፈጠርንም። ቢሆንም የምንፈልገውን አግኝተናል። አሁንም ግን በማጥቃቱ ላይ ጠንክረን መስራት እንዳለብን ይሰማኛል። ከራሳችን የሜዳ ክፍል ስንወጣ ብዙ ችግር የለብንም። ሆኖም ግን የሜዳው የመጨረሻ ክፍል ላይ ተጨዋቾቻችን የኳስ ግንኙነታቸው ደካማ ነው። እዛ ላይ ጠንክረን መስራት አለብን። ጨዋታዎችን ሁሉ ማሸንፍ እንፈልጋለን ለዛ ድግሞ ብዙ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ይኖርብናል። ”
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም – አርባምንጭ ከተማ
” አሸንፈን ለመውጣት የተጠቀምነው ስትራቴጂ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ አርባ ደቂቃዎች አተገባበራችን የተሻለ ነበር። የገባብን ኳስም በተከላካይ የተጨረፈ ነበር። በራሳችን ሜዳ ላይ የነበረው ሰው በሰው የመያዝ ስህተት ዋጋ አስከፍሎናል ማለት እችላለው። እንደ ቡድን ግን ክፍተቶችን በመዝጋቱ በኩል ቡድናችን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ጥሩ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ልምዳቸውን እና የአጨራረስ ብቃታቸውን ተጠቅመው አሸንፈውናል። ውጤቱን በፀጋ ተቀብልነዋል። ”