በጨዋታዎች መሰረዝ (መዘዋወር)፣ በሜዳ ውጭ ባሉ ሁከቶች እንዲሁም በአሰልጣኞች መቀያየር (ሳይናገሩ መሰወር) ተከቦ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 መርሃ ግብር 8ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል::
እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው በ8 ጨዋታዎች 21 ግቦች የታዩበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ8ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ግን አዝናኝ ሆኖ አልፏል። ይህም እስከ 7ኛ ሳምንት ድረስ በግብ ድርቅ ተመትቶ የነበረውን ሊግ ነፍስ ዘርቶበታል:: አምና በ24ኛው ሳምንት ከተመዘገበው 24 ጎል በኋላ ከፍተኛ የሆነው የግብ መጠን በዚህ ሳምንት ተመዘረግቧል።
ለመሆኑ ካሳለፍነው ሳምንት በፊት በነበሩ ጨዋታዎች ምን ያህል የግብ ድርቀት ነበር የሚለውን በቁጥሮች አስደግፈን እንመልከት።
እስከ 7ኛው ሳምንት መደረግ ከነበረባቸው 58 ጨዋታዎች 51 ተደርገዋል::
የተቆጠሩ ግቦች- 77
በአማካይ በአንድ ጨዋታ የሚቆጠሩ ግቦች ብዛት- 1.5
ያለምንም ግብ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ብዛት- 14 (27%)
አንድ ግብ ብቻ የታየባቸው ጨዋታዎች ብዛት- 13 (25%)
ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ብዛት – 55
ከላይ የተዘረዘሩትን አሃዛዊ መረጃዎች ስናጤን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት (52%)የኢትዮጵያ ፕሪምየር ጨዋታዎች ወይ 0-0 አልያም 1-0 የሚጠናቀቁ ናቸው ።
በዚህ ሳምንት ግን በአማካይ 2.63 ግቦች ሲታዪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ጨዋታ ብቸኛው ግብ ያልተቆጠረበት ፍልሚያ ሆኖ አልፏል።
እስከ 7ኛ ሳምንት ድረስ ግቦች ብርቅ እንዲሆኑብን ያደረጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ለዚህ ጥያቄ በርካታ መልሶች መመለስ ይቻላል። የማጥቃት እንቅስቃሴን ቀላል የሚያደርጉ ሜዳዎች አለመኖር ፣ የአብዛኞቹ ቡድኖች የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይ የሚታይ በጥልቀት የመከላከል አቀራረብ እና ከጥቂት ክለቦች ውጪ በአመዛኞቹ ላይ የሚታይ ግልፅ የማጥቃት ስትራቴጂ አለመኖር እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። ከሁሉም በላይ ግን ጎል ማስቆጠር የአጥቂዎች ተግባር ብቻ ተደርጎ መወሰዱ ጎል ማስቆጠርን በአጥቂዎች ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል።
በሊጉ ባለፉት አመታት በተከታታይ እና በወጥነት ጎል የሚያስቆጥሩ አጥቂዎቻችን በቁጥር ጥቂት ናቸው። በዚህም ጎል የማስቆጠር ሀላፊነት በብቸኝነት የተጣለባቸው አጥቂዎቻቸን ድክመት ጎልቶ ይታያል።
1) የአጥቂዎች ደካማ የቦታ አያያዝ ወይንም ራስን ከተጋጣሚ ተከላካዮች ነፃ አድርጎ ኳስን በተሻለ የግብ ማግባት ቦታ አለመቀበል::
2) በአጥቂዎች እና በጣም ወደ ኃላ ተስበው በሚጫወቱት አማካዮች መካከል ያለው ሰፊ ክፍተትን ተከትሎ ከቡድኑ እንቅስቃሴ መነጠል።
3) ለአጥቂዎች የሚደርሱ ኳሶች ጥራት እጥረት እና ለተፈለገው ሰው አለመድረስ
4) የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት ሂደት ላይ ያላቸው እጅግ ዝቅተኘመ ተሳትፎ
5) የአጥቂዎች እና የአጥቂ አማካዮች የተጋጣሚን የተከላካይ አጥር በግል ብቃት ማፈራረስ የሚያስችል ክህሎት እና ተነሳሽነት አለመኖር።
በ8ኛ ሳምንት ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?
አብዛኛዎቹ ክለቦች በተለይ ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከምንም በላይ ተከላክሎ አና ውጤትን አስጠብቆ መውጣት ዋንኛ አላማቸው ነው። ይህ ደግሞ ወደ ኃላ አፈግፍገው እንዲጫወቱ እና በማጥቃት ወረዳ በቁጥር አንሰው እንዲያጠቁ ግድታ ውስጥ ያስገባቸዋል:: ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ዋንኛው መንስኤ ደግሞ ይሄ ነው። ይህ ችግር በአብዛኛው ከሜዳ ውጪ በሚጫወቱ ክለቦች ላይ ይስተዋላል:: በደጋፊዎች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶአቸው ነገር ግን ባዶ ለ ባዶ የተጠናቀቁትን ደደቢት ከ ፋሲል ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትየጵያዊያ ቡና ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ለአብነት እንመልከት።
ፋሲል ከተማ ከደደቢት ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ጨዋታ ፊሊፕ ዳውዚ እና ራምኬል ሎክ ከቀሪው ቡድናቸው በመነጠላቸው እና ተገቢ የሆነ እድል ባለማግኘታቸው ሲቸገሩ አስተውለናል። እንደ ፋሲል ሁሉ ጌታነህ ከበደ ከቡድን አጋሮቹ በቂ ድጋፍ ባለማግኘቱ ጨዎታ መሃል ቅሬታ ሲያሰማ አስተውልናል።
ብዙ ተውርቶለት የነበረው የሸገር ደርቢም ብዙ ሙከራን ሳያስተናግድ ተቋጭቷል። ከግጥሚያው ይልቅ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ያሳዩት ህብረ ቀለማዊ እና ማራኪ ድጋፍ አስደስቶን አልፏል።
ነገር ግን ሳምንታት እየገፋ በመጡና ክለቦቹ ነጥብ የመሰብሰብ ግዴታ ውስጥ ሲገቡ ማጥቃታን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ይህንም ተከትሎ የጨዋታ መከፈት እንዲሁም የግቦች በርከት ማለት ይመጣል። በዚህ ሳምንትም የተመለከትነው ይህንን ነው።
ሆኖም ክለቦች ለማጥቃት የሚሰጡትን ቦታ እስካላሳደጉ እና አወንታዊ አጨዎወትን (proactive football) እስካልተገበሩ ድረስ አሰልቺ እና ግብ አልባ ጨዎታዎችን ለማየት መገደዳችን ነው። ስለዚህ እንደ 8ኛ ሳምንት አይነት በጎል የተንበሸበሹ ማራኪ ግጥሚያዎች ይብዙልን እያልኩ ፅሁፌን አገባደድኩ።