የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት እና የማጠቃለያ ፕሮግራም የዘገየበትን ምክንያት የሊጉ አክሲዮን ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ ምላሽ ሰጥተውበታል።
ያለፉትን ሁለት ዓመታት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ እና የኮኮቦች ሽልማት ፕሮግራም የሊጉ ውድድር በተጠናቀቀ ከቀናቶች በኋላ በደማቅ ስነ ስርዓት ይካሄድ እንደነበረ ይታወሳል። የዘንድሮ የሽልማት እና የመዝጊያ መርሐ ግብር ግን ባልተለመደ ሁኔታ ሊጉ ከተጠናቀቀ እነሆ አንድ ወር ቢሆነውም እስካሁን ሳይካሄድ ቀርቷል። በዚህም መነሻነት በብዙ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል። ይህን ተከትሎ እስካሁን ያለመካሄዱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል ስንል የሊጉ አክስዮን ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈን ስለ ጉዳዮ አናግረን ተከታዮን ምላሽ ሰጥተውናል።
ስለዘገየበት ምክንያት…
እንደሚታወቀው ይን ፕሮግራም የሚያዘጋጀው በውላችን መሰረት ሱፐር ስፖርት ነው። አጠቃለይ ለፕሮግራሙ የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍነው ይሄ ተቋም ነው። ከእኛ የሚጠበቀው ለአስራ ስድስቱም ክለቦች በየደረጃቸው የሚያገኙትን የገንዘብ አከፋፈል ስርዓት ነው። እኛ ከፍለን ጨርሰናል። አሁን ሱፐር ስፖርት የስም ሽያጭ ለውጥ ሊያደርግ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአዲስ ድርጅት ጋር ለመስራት ሂደቶች እያደረገ ነው። ይህን ማጠናቀቅ ባለመቻሉ የኮከብ ሽልማቱ ሊዘገይ ችሏል።
የስም ለውጡ ምን ከሚባል ተቋም ጋር ነው? በተለያዩ መንገዶች በባንክ ዘርፍ ያለ ተቋም ስያሜውን ሊወስድ እንደሆነ ይሰማል።
አሁን እኔ ተነስቼ ሳይዋዋሉ ከእከሌ ተቋም ጋር ነው ልል አልችልም። የተለያዩ ነገሮች ይነሳሉ ይህ ሀሰት ነው። ስምምነቱ ሳይጠናቀቅ ሳይዋዋሉ እከሌ ነው ብሎ መናገር ከባድ ነው። ነገሩ ሂደት ላይ ነው ፤ ሲጠናቀቅ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።
የ2015 የኮከቦች ሽልማት ታዲያ መቼ ይካሄዳል…
በእርግጠኝነት በዚህ ቀን ይካሄዳል ብሎ መናገር አይቻልም ፤ የስም ሽያጩ ሂደት ላይ ነው። ነገሮች ሲጠናቀቁ መርሐግብሩ የሚካሄድበትን ሁኔታ ይመቻቻል። ሆኖም ትንሽ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ዋናው ነገር አዲስ ከሚዋዋለው ድርጅት ጋር ስምምነቱ ሲጠናቀቅ የኮከብ ሽልማቱን አንድ ላይ አብሮ ይፋ እንዲደረግ ዕቅድ አድርገው ነው። ስለዚህ ቀኑ ገና አልተወሰነም።