በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውሩ የገቡት ሻሸመኔ ከተማዎች የከፍተኛ ሊግ ጎል አስቆጣሪውን አጥቂ እና የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹን ሲያስፈርሙ የሁለት ነባሮችን ውል አድሰዋል።
በፕሪምየር ሊጉ ላይ ከ15 የውድድር ዓመታት በኋላ የሚሳተፈው ሻሸመኔ ከተማ ከሰዓታት በፊት አጥቂው እዮብ ገብረማርያምን ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቀቀውን አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ እና የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቻላቸው መንበሩን ስለማስፈረሙ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ ጠቁሟል።
የክለቡ አዲስ ፈራሚ የሆነው ቻላቸው መንበሩ በደሴ ከተማ ፣ ገላን ከተማ እንዲሁም ከ2014 እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ በኢትዮጵያ መድን በመስመር ተከላካይነት ሲጫወት ቆይቶ ሻሸመኔን ተቀላቅሏል። ሦስተኛው ተጫዋች ሙሉቀን ታሪኩ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ለአዲስ አበባ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል። በ14 ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከነማ አጥቂ በአንድ ዓመት ውል የሻሸመኔ ከተማ ተጫዋች ሆኗል።
ከአዲስ ፈራሚዎቹ ባሻገር ክለቡ አመሻሹን የሁለት ነባሮችን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል። ቡድኑን በአምበልነት እና በአማካይነት በከፍተኛ ሊጉ ያገለገለው የቀድሞው የመድን ተጫዋች ጌትነት ተስፋዬ እና በአቃቂ ቃሊቲ እንዲሁም በመድን ተጫውቶ ያሳለፈው አብዱልቃድር ናስር ለተጨማሪ ዓመት ውላቸው የተራዘሙት ተጫዋቾች ናቸው።