በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ የመጀመርያ ክልል አቀፍ ውድድር ሊዘጋጅ ነው

የትግራይ ዋንጫ ውድድር ሊዘጋጅ መሆኑን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።

በ2011 ጅማሮውን አድርጎ ለሦስት ዓመታት ከተካሄደ በኋላ በጦርነቱ ምክንያት ሳይደረግ የቆየው የትግራይ ክልል ዋንጫ ዳግም ሊጀመር እንደሆነ አወዳዳሪው አካል ዛሬ በመቐለ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫው እንደተገለፀው ውድድሩ ከነሐሴ 20 እስከ ጳጉሜን 4 እንደሚካሄድ እና አስራ ሁለት ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል።

በቀጣይ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ እንዲሳተፉ ውሳኔ የተሰጠባቸው ወልዋሎ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ስሑል ሽረ፤ እንዲሁም በብሄራዊ ሊግ እንዲሳተፉ የተወሰነው ደደቢት፣ አክሱም እና ሶሎዳ ዓድዋን ጨምሮ ዋልታ ፖሊስ ትግራይ፣ ትግራይ ውሀ ስራዎች ድርጅት፣ ራያ ዓዘቦ፣ ፈራውን እና ሓውዜን በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

ሸቶ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከትግራይ ክልል እግርኳስ ፌደሬሽን በጋራ የሚዘጋጀው ይህ ውድድር በትግራይ ስታዲየም እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ገልፀዋል።