የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ዳግም ሊታደስ ነው

የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ አርቴፊሻል ሳር እንዲሆን እንደተወሰነ ይፋ ሆኗል።

በአሁኑ ሰዓት በየ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ፕሮግራም እና የኮከቦች ሽልማት መርሐ-ግብር እየተከናወነ ይገኛል። በመርሐ-ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የመክፈቻ ንግግር እያደረጉ ከሚገኙት የዕለቱ የክብር እንግዶችን መካከል የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ይገኛሉ። ሚኒስተሩ ካነሷቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል የሜዳ እድሳት ሀሳቦች ሲሆኑ ከደቂቃዎች በፊት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከታኅሣሥ ወር የመጨረሻ ቀናት በኋላ ሊጉ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚመለስ መግለፃቸውን አስነብበናል።

በንግግራቸው የመቶ አለቃ ፍቃደን ሀሳብ ያጠናከሩት አቶ ቀጀላ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው መጠነኛ ጥያቄዎች ያሉበት የመጫወቻ ሜዳው ጉዳይ ላይ ዳግም እድሳት እንደሚደረግ አመላክተዋል። በዚህም የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ አርቴፊሻል ሳር እንዲተከልበት እንደተወሰነ ይፋ አድርገዋል።