የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሽልማቱን ከተረከበ በኋላ ምን አለ?

የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ኮከብ በመባል የተመረጠው ቢኒያም በላይ ሽልማቱን ከተረከበ በኋላ ተከታዩን ሀሳብ አጋርቷል።

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የኮከቦች ሽልማት በአሁኑ ሰዓት በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በመከናወን ላይ ይገኛል። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሊጉ ኮከብ ተጫዋችን ሽልማት ቢኒያም በላይ ማሸነፉን ከደቂቃዎች በፊት የገለፅን ሲሆን ተጫዋቹም ከክብር እንግዳው አንዋር ሲራጅ እጅ ሽልማቱን ከተረከበ በኋላ ተከታዩን አጭር ንግግር ከመድረኩ ሳይወርድ አሰምቷል።

“መላው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰዎች፣ የበላይ አካሎች ፣ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት 16ኛውን ዋንጫ ስንወስድ ቀላል ዓመት አይደለም ያሳለፍነው ፤ በጣም ከባድ የውድድር ዓመት ነበር ያሳለፍነው። ይሄን ሁሉ ማሳካት የቻልነው ደግሞ በህብረታችን ነው እና በድጋሚ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተሰቦች 16ኛውን ዋንጫችንን ወደ ቤቱ አስገብተናልና እንኳን ደስ ያላችሁ።

“ይህ ነገር እንዲሳካ እንግዲህ አሰልጣኞቻችን ዓመቱን ሙሉ እጅግ አርገው ነው የለፉት እና የልፋታችሁን የድካማችሁን ዓመቱን ሙሉ የለፋንበትን በስኬት አጠናቀን ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ በመገኛታችን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ተጫዋቾች ወንድሞቼ ጓደኞቼ ዓመቱን ሙሉ ለቡድናችን በህብረት የቻልነውን ሁሉ ነገር አድርገናል። ዛሬ እኔ እዚህ መድረክ ላይ ልቁም እንጂ ሁላችሁም የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ካደረግነው ነገር አንፃር እዚህ መድረክ ላይ ብንመጣ እና ብንገኝ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ዛሬ እኔ እዚህ መጥቼ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወክዬ ኮከብ ተጫዋች ተብዬ ስለተመረጥኩ እጅግ አድርጌ ጓደኞቼን አመሰግናለሁ። ያለእናንተ ልፋት ያለእናንተ ድካም እዚህ መቆም አልችልም እና እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

“በመቀጠል እንግዲህ ድምፅ ሲሰጥ የሁሉም ህዝብ አለ እና ደጋፊያችን የሆኑ አሉ ፤ እኛን የማይደግፉ የተለያዩ የእግርኳስ ቤተሰቦች አሉ እና ዘንድሮ ኮከብ ተጫዋች ሆኜ እንድመረጥ ድምፃችሁን የሰጣችሁኝን ሁሉ አመሰግናለሁ። ቤተሰቦቼ ባለቤቴ የልጆቼ እናት ይን ሁሉ ነገር ለማሳካት በቅቻለሁ እና እንኳን ደስ ያለሽ።”