በጀርመን ሊጎች በመጫወት ላይ ከሚገኙት በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ሁለቱ በአዲስ ክለብ የውድድር ዓመቱን ጀምረዋል።
በጀርመን ታችኛው ሊጎች የሚጫወቱ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውን በአዲሱ የውድድር ዓመት በአዲስ ክለብ ብቅ ብለዋል። የመጀመርያው የሀያ ዓመቱ የአጥቂ አማካይ አዲል መሐመድ ዘነበ ነው። የእግር ኳስ ሂወቱ Vellmar በተባለ ክለብ ጀምሮ ለአምስት ዓመታት በክለቡ የታዳጊ ቡድኖች ቆይታ የነበረው ይህ ተጫዋች እናት ክለቡን ከለቀቀ በኋላ ለአንድ የውድድር ዓመት VfL Kassel በተባለ ክለብ ተጫውቷል። አሁን ደግሞ እዛው በጀርመን Bezirksoberliga ተሳታፊ ለሆነ Tuspo Grebenstein የተባለ ክለብ ለመጫወት ፌርማውን አኑሯል።
ሌላው በአዲሱ የውድድር ዓመት በአዲስ ክለብ ብቅ ያለው የሀያ ሥስት ዓመቱ አጥቂ ሚካኤል ነዋይ ነው። የእግር ኳስ ሂወቱ RW Walldorf በተባለ ክለብ የጀመረው ይህ ሁለገብ ተጫዋች ከአጥቂነት በተጨማሪ የመስመር ተጫዋች ሆኖ መጫወትም ይችላል። በአዲሱ የውድድር ዓመትም አሳዳጊ ክለቡን ለቆ በ Hessenliga የሚሳተፈውን
FC Eddersheim ለተባለ ክለብ ለመጫወት ፌርማውን አኑሯል።
በተያያዘ ዜና በአንድ ወቅት ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የላይብዚክ ኣካዳሚ ውጤት የሆነው ተከላካይ አማካዩ ናኦድ መኮንን በአሁኑ ሰዓት ክለብ አልባ ሆኖ ሲገኝ ሌላው በጀርመን ታችኛው ሊግ በመጫወት ላይ የሚገኘው አጥቂው ሻምበል ጌትነት Germania Wiesbaden ለተባለ ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል።