ከሜዳቸው ውጪ በባህር ዳር ከተማ 2ለ1 የተረቱት የአዛም አሠልጣኝ ብሩኖ ፌሪ ከጨዋታው በኋላ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተውናል።
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። የመጀመርያው አጋማሽ እና ሁለተኛው አጋማሽ። የመጀመርያው ግማሽ ለእኛ ከባድ ነበር። እንዴት እንደምገልፀው አላቅም። በውድድር ዓመቱ አንድ ይፋዊ ጨዋታ ብቻ ነው ያደረግነው፤ እሱም ሙሉ ዘጠና ደቂቃ አልነበረም፤ ገና በሀያኛው ደቂቃ ያለቀ ጨዋታ ነበር። ችግራችን የጨዋታ ፍጥነት ነበር፤ በመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታችን ፍጥነት አልነበረውም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ለማሻሻል ሞክረናል። በተሻለ ፍጥነት ተጫውተን ተጋጣምያችን ላይ ጫና ማሳደር ችለናል። በሁለተኛው አጋማች ጥሩ ተጫውተዋል ተጨማሪ ጎልም ማስቆጠር እንችል ነበር። የመጀመርያው ዙር ተጠናቋል በሁለተኛው ዙር እድል አለን ፤ ከዚህ ጨዋታም ትምህርት እንወስዳለን።
ስለተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ
ጥሩ ቡድን እንደምንገጥም እናውቅ ነበር። የባለፈው ዓመት ጨዋታዎቻቸው ለመመከት ጥረት አድርገን ነበር። ዛሬ እንዳየነውም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሏቸው። ቀጣይ እቅዳችን በሜዳችን በምናደረገው ጨዋታ ጠንክሮ ለመቅረብ ነው። የመዘጋጃ አምስት ቀናት አሉን። እርግጥ ነው ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ጠንካራ ቡድን ነው የምንገጥመው። ግን ጨዋታው በሜዳችን እስከሆነ ድረስ ጫና ፈጥረን ጎል አስቆጥረን ለማሸነፍ የተቻለንን እናደርጋለን።
ስለ ቡድናቸው
ችግሩ የተጫዋች ጥራት ላይ አይደለም፤ ዛሬ የነበረን ችግር ቴክኒካል ኳሊቲ አይደለም። አንዳንድ ተጫዋቾቻችን ላይ የጫና ስሜት ነበር፤ ይሄም ሰዋዊ ነው። ይህ አስተካክለን እንመለሳለን። ምክንያቱም በዚህ ውድድር ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ በጫና ውስጥ ሆኖ መጫወትን መልመድ አለብን። ዛሬ ግን እሱ ብቻ አደለም ምክንያቱም በስቴድየም ውስጥ ደጋፊ አልነበረም። በቀጣይ በደጋፍያችን ፊት የምናደርገው ጨዋታ ላይ ግን ከመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጀምረን ጫና ፈጥረን ለመጫወት እንሞክራለን። ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ አርባ አምስት ደቂቃ ብቻ ጥሩ መጫወት በቂ አደለም። ቀጣይ ግን ተሽለን እንቀርባለን ፤ አማራጭም የለንም።