በትግራይ ክልል የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ

በትግራይ ክልል ለመጀመርያ ጊዜ የ’D’ ላይሰንስ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ።


በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የተለያዩ ስልጠናዎች ያመለጣቸውን በትግራይ የሚገኙ አሰልጣኞች ለማብቃት አልሞ የተዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በመቐለ ከተማ ተጀምሯል። የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ፣ ኢንስትራክተር መሰረት ማኔ እና የክልሉ ብቸኛ ሴት ኢንስትራክተር ሂወት አረፋይነ የሚመራው ይህ የካፍ ‘D’ ላይሰንስ ስልጠና በተከታታይ ለአስራ አንድ ቀናት ይሰጣል። የቀደሞ ተጫዋቾች እና ጀማሪ አሰልጣኞች የሚገኙበት ስልጠና ከስልሣ በላይ ሰልጣኞች ያካተተ ሲሆን በክልሉ ሲካሄድም የመጀመርያው ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራሮች ከወራት በፊት በገቡትን ቃል መሰረት ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ይህ ስልጠና ማዘጋጀታቸው በመድረኩ ተመስግነዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኢንስትራክተር ሂወት አረፋይነ ለስልጠናው መሳካት ላደረገችው ጥረት ከመድረኩ ላቅ ያለ ምስጋና ተችሯታል።

ስልጠናው በተከታታይ ለአስራ አንድ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን የክፍል እና የሜዳ ላይ ስልጠናዎች ያካተተ ነው። ስልጠናው በክልሉ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ ብቁ የታዳጊዎች ስልጠና እጥረት በተወሰነ መልኩ ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።