የካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታዎች መካከል አንዱን ለመምራት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ተመርጠዋል።
የአህጉራችን ሁለተኛው ትልቁ የክለቦች ውድድር የሆነው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ማስተናገድ ጀምሯል። በዋናው ውድድር የሚሳተፉ አነስተኛ ደረጃ ያላቸው ክለቦች ከሚያደርጓቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል ዛሬ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም የዛንዚባሩ ጄ ኬ ዩ ኤስ ሲ ዜድ እና የታንዛኒያው ሲንጊዳ ቢግ ስታርስ የሚያደርጉት ጨዋታ አንዱ ነው።
ይህ በአዛም ኮምፕሌክስ የሚደረገውን ጨዋታ ደግሞ በዋና እና በረዳት ዳኝነት አራት የሀገራችን ዳኞች እንደሚመሩት ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። በዚህም ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሐል፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በመስመር እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።
የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ ጨዋታ ከቀናት በፊት ተከናውኖ በሲንጊዳ 4ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።