👉”እውነት ለመናገር የዳኝነት ችግሮችን መቋቋም አልቻልንም ፤ ዳኞቹ አለቆቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ በደል ይፈፅሙብሀል”
👉”…ከተቻለ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለፍፃሜው ጨዋታ ወደዚህ እንዲመጡ ጥሪ አቀርባለው”
👉”…ይሄ የሆነው አንድም የተጫዋቾቼ ብቃት የተመጣጠነ ስለሆነ ነው”
በምስራቅ አፍሪካ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምድቡን በበላይነት ካጠናቀቀ በኋላ በትናንትናው ዕለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታውን ከኬንያው ቪጋ ኩዊንስ ጋር አከናውኖ 2ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወቃል። በዋናው አህጉራዊ የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚያሳትፈውን ትኬት ለመቁረጥም ከነገ በስትያ ወሳኝ የፍፃሜ ጨዋታውን ከታንዛኒያው ጄቲኬ ኩዊንስ ጋር ያደርጋል።
በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ በውድድሩ ተሳትፎ ለሁለተኛ ጊዜ ለፍፃሜ የደረሰውን ባንክ የሚመሩት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከትናንቱ ተጋድሎ ከነበረው ጨዋታ በኋላ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።
የቡድኑ ህብረት ለፍፃሜ እንዲደርሱ እንዳደረገ የሚናገሩት አሠልጣኝ ብርሃኑ ለተጫዋቾች፣ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት እና ለንግድ ባንክ አመራሮች ከፍ ያለ ምስጋና እንደሚገባ በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል።
“ውድድሩ በጣም ጠንካራ ነው። ወደ ስፍራው ይዘን የሄድናቸውን ሁሉንም ተጫዋቾች እስካሁን ባለው ጨዋታ ተጠቅመናል። ያልተጫወተ አንድም ተጫዋች የለም። ይሄ የሆነው አንድም የተጫዋቾቼ ብቃት የተመጣጠነ ስለሆነ ነው።”
በውድድሩ የዳኝነት ችግር እጅግ እየፈተናቸው እንደሆነ የተናገሩት የቡድኑ አሠልጣኝ ይህ ህፀፅ በፍፃሜው ጨዋታም ዋጋ እንዳያስከፍላቸው የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
“በትናንቱ የቬጋ ኩዊንስ ጨዋታ ከፍተኛ የዳኝነት በደል ነበር። በምድብ ጨዋታዎችም ችግሮች ነበሩ ግን ዓምናም ሆነ ዘንድሮ አራት ውስጥ ስንገባ ነው ችግሮቹ እየተባባሱ የሚመጡት። እውነት ለመናገር የዳኝነት ችግሮችን መቋቋም አልቻልንም። ዳኞቹ ሲጠቃቀሱ አይተናል ፤ በተጨማሪም ያገባነውን ንፁህ ጎልም ሲሽሩብንና ተጫዋቾቻችን ላይ በካርድ እና በቁጣ ጫናዎች ለመፍጠር ሲሞክሩ ይስተዋላል። ይህ ፈፅሞ ልክ አይደለም።” ካሉ በኋላ የሴካፋ የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ለሆኑት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ጥሪ አስተላልፈዋል።
“ከኢትዮጵያ ወደ ዩጋንዳ ለመምጣት የሽኝት ግብዧ ሲደረግልን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ‘የውድድሩ ሰብሳቢ እኔ ነኝ’ ብለውን ‘ከጎናችሁ አለሁ’ በማለት ቃል ገብተውልን ነበር። እሳቸው እዚህ ከመጡ እርግጠኛ ነኝ የዳኝነት ጫናው ይቀንስልናል። በዚህ አጋጣሚ ከተቻለ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለፍፃሜው ጨዋታ ወደዚህ እንዲመጡ ጥሪ አቀርባለው ፤ ድጋፍ ያስፈልገናል። የሌላው ሀገር እግርኳስ ፌዴሬሽን በእያንዳንዱ ነገር ላይ እገዛ ሲያደርግ ይታያል። ይህ ውጤት ለሀገራችን እግርኳስም ጥሩ ነው ብዬ ስለማስብ ድጋፍ እንዲደረግልንና እሳቸው መጥተው እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለው። እዚህ ከሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ውጪ ማንም የለንም። ኮሚቴው በሙሉ በዩጋንዳዊያን የተሞላ ነው። ታንዛኒያዎችም ኬኒያዎችም እንደዛው። ሱማሊያ እንኳን በአቅሟ አላት። ዳኞቹ አለቆቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ በደል ይፈፅሙብሀል።” ብለው የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲያደርግ በአፅኖት ተናግረዋል።
በመጨረሻም በዩጋንዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከአንድም ሁለት ጊዜ ቡድኑን ለማነቃቃት የእራት ግብዣ እንዳደረጉላቸው እንዲሁም በየጨዋታው ስታዲየም እየተገኙ እንደሚያበረታቷቸው በመግለፅ ምስጋናቸውን በክለቡ ስም አስተላልፈዋል።