“እውነት ለመናገር እጠራለው ብዬ አልጠበኩትም” ፍፁም ጥላሁን

ስለብሔራዊ ቡድን የመጀመርያው ጥሪው ፍፁም ጥላሁን ይናገራል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን አንስቶ በኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን እና ዋናው ቡድን አድጎ መጫወት የቻለው ፍፁም ጥላውን በ2013 ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ጥሩ ውድድር በማሳለፍ በዚህ ዓመት ለጣና ሞገዶቹ ፊርማውን በማኖር ሲጫወት ቆይቷል። በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታውን ከግብፅ ጋር የሚያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ የቀረበለት ፍፁም ጥላሁን በብሔራዊ ቡድን መመረጡ የፈጠረበትን ስሜት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፎበት ስለነበረው አዲስ አበባ ከነማ…

አዲስ አበባ ከተማ የነበረኝ ቆይታ ለእኔ ዳግም የተወለድኩበት ቤት ነው ማለት የምችለው። ብዙ ትልቅ ነገር ያገኘሁበት ነው። በእግርኳስ ተስፋ ቆርጬ ባለበት ወቅት ነው አዲስ አበባ በመጫወቴ እራሴን ለማሳየት እንድችል፣ ትልቅ ተስፋ እንዲኖረኝ እና አሁን ለደረስኩበት የእግርኳስ ህይወቴ መነሻ የሆነኝ ቤት በመሆኑ ለአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ትልቅ አክብሮት አለኝ።

በባህር ዳር የመጀመርያ ዓመት የተጠበቀውን ያህል ስላልሆነበት ምክንያት…

አዎ የሚጠበቅብኝን ያህል ግልጋሎት እንዳልሰጠው አስባለው። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። አንደኛ ባህር ዳር እንደ አዲስ አበባ ከተማ አይደለም። በየጨዋታው ማሸነፍ ይኖርብሀል። ደጋፊውም ውጤት ይፈልጋል። ትንሽ ጫናዎች ነበሩ። አዲስ ቡድን እንደመሆኑ መጠን በፍጥነት መላመድ አልቻልኩም ነበር። በአጠቃላይ የታሰበውን ያህል ባይሆንም በምችለው አቅም ቡድኔን ለማገዝ ጥረት አድርጌ አለው። በቀጣይ ዓመት በመጨረሻው ያጣነውን ዋንጫ ለማግኘት ከቡድን አጋሮቼ ጋር የምችለውን ሁሉ ለማድረግ እጥራለው።

በኢንተርናሽናል መድረክ ለመጀመርያ ጊዜ ስላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች…

እውነት ለመናገር ባህር ዳር ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፉ በጣም ደስ ብሎኛል። ይህ ለክለቡ በአፍሪካ መድረክ ሀገርን በመወከል የመጀመርያው ተሳትፎ ነው። በቂ ዝግጅት ሳናደርግ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ቡድን የሚባለውን አዛምን በሜዳችን እና ከሜዳ ውጭ አሸንፈን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋችን አስደሳች ነው። እኔም በግሌ በኢንተርናሽናል ጨዋታ የመጀመርያዬን ሁለት ጎሎች በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል።


ስለ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ…

እውነት ለመናገር እጠራለው ብዬ አልጠበኩትም ፤ አላሰብኩትም ነበር። በካፍ ኮንፌዴሬሽን ጨዋታ ወቅት ያሳየሁት እንቅስቃሴ አስመርጦኛል ብዬ አስባለው። የሁሉም ተጫዋች ህልሙ ለሀገሩ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ነው። ይህን ህልሜን በመሳካቱ ደስ ብሎኛል። ሀገሬንም በምችለው አቅም ለማገልገል እፈልጋል።

በድጋሚ በብሔራዊ ቡድን ስለመመረጥ…

በመጀመርያ ይህን ዕድል መጠቀም እንዳለብኝ አምናለው። በቀጣይ በተደጋጋሚ በብሔራዊ ቡድን ለመጠራት ጠንክሬ መስራት እንዳለብኝ ነው የማስበው።