ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የወረደው አርባምንጭ ከተማ ለቀጣዩ የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው ጊዜያዊ አሰልጣኙን በዋና ኃላፊነት ሲቀጥር የሦስት ነባሮችን ውል አራዝሟል።
በ2014 ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መመለስ ችሎ ሁለት የውድድር ዘመናትን በሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ ዕርከን ላይ መሳተፍ ከቻለ በኋላ ከሊጉ ለመውረድ የተገደደው አርባምንጭ ከተማ ለቀጣዩ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ላይ ስለሚኖረው ተሳትፎ ከወዲሁ ወደ ሥራ በመግባት ጊዜያዊ አሰልጣኝ የነበረውን በረከት ደሙን በዋና ኃላፊነት ሲሾም የሦስት ነባሮችን ውል አራዝሟል።
አሰልጣኝ በረከት ደሙ የተጫዋችነት ዘመኑን በአርባምንጭ ከተማ ውስጥ ካገባደደ በኋላ በመቀጠል በ2009 እና 2010 ክለቡን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የመራው በረከት የአርባምንጭን ከ20 ዓመት በታች ቡድን በ2015 ሲመራ ቆይቶ የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን መሰናበት ተከትሎ ክለቡን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ቢመራም ክለቡ ከሊጉ መውረዱ ይታወሳል። አሰልጣኙ በቀጣዩ ዓመት ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ የመመለስ አስገዳጅ ህግ በተቀመጠለት ውል ክለቡን ለቀጣየቹ ሁለት ዓመታት እንዲመራ ክለቡ ሾሞታል።
ከአሰልጣኝ በረከት ሹመት በተጨማሪ ክለቡ ለረጅም ዓመታት በክለቡ በመስመር ተከላካይ እና በአምበልነት ያገለገለውን የወርቅይታደስ አበበን ፣ የተከላካይ አማካዩን አንዱአለም አስናቀ እና የአማካዩ መሪሁን መስቀሌን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።