በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ የተደረገለት ራምኬል ጀምስ ስለ ጥሪው ይናገራል።
በትውልድ ስፍራው ጋምቤላ ከተማ እግር ኳስን በክለብ ደረጃ በመጫወት የጀመረው እና በአንደኛ ሊግ እና በከፍተኛ ሊግ ለሁለት ዓመታት በጉለሌ ክፍለ ከተማን በአንበልነት የተጫወተው ራምኬል ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀል በፕሪሚየር ሊጉ ሲጫወት መቆየቱ ይታወሳል። በቀጣይ ጳጉሜ ወር ከግብፅ ጋር በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታውን በሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ውስጥ ራምኬሎ ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ ቀርቦለታል። ድረ ገፃችንም ይህን ጥሪ አስመልክቶ ከራምኬል ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።
በኢትዮጵያ ቡና ስላሳለፈው ጊዜ…
“ለሊጉ አዲስ ነኝ እንዲሁም ቡድናችን ብዙም ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ባለመዋቀሩ ትንሽ ተቸግረን ነበር። ሊጉም በጣም አሪፍ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት በመሆኑ በጣም አሪፍ ነው። በተለይ እኔ ገና ልጅ ነኝ ብዙም ልምድ የሌለኝ ስለሆነ የመጀመርያ አምስት ጨዋታዎች በጣም ፈትኖኝ ተቸግሬ ነበር። በኋላ ነው በተወሰነ መልኩ እየለመድኩኝ የመጣሁት። በአጠቃላይ ብዙ ነገር የተማርኩበት ልምድ የወሰድኩበት ለቀጣይ የውድድር ጊዜ ትኩረት አድርጌ መስራት እንዳለብኝ ነው የማስበው።
ስለ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ…
“በጣም ነው ደስ ያለኝ ፈጣሪዬን አመሰግናለው። አሰልጣኝ ዳንኤልም ይህን ዕድል ስለሰጠኝ በጣም አመሰግናለው። ክለቤንም ኢትዮጵያ ቡናን እንዲሁ አመሰግናለው። ትናንት የመጀመርያ የብሔራዊ ቡድን ልምምዴን አድርጌ አለው። ብዙ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር አብሬ መስራት ችያለሁ ከእነርሱም ብዙ ነገር ስማር ነው የቆየሁት ይህ በጣም ደስ ይላል። እንደምታቁት አንድ ዓመት አንደኛ ሊግ ቆይታ አድርጌ በመቀጠል ከፍተኛ ሊግ ገብቼ ተጫወትኩ በዓመቱ ደግሞ ፕሪሚየር ሊግ ለመጫወት በቃሁኝ አሁን ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ተጠራሁኝ ይህ ልዮ ደስታ ፈጥሮብኛል። ሀገርን ከማገልገል የበለጠ ምንም ነገር የለም። በጣም ደስ ብሎኛል።
ስለቀጣይ ጉዞው…
“ዋናው ነገር ለመጀመርያ ጊዜ በመጠራቴ ብቻ መቆም እንደሌለብኝ አውቃለው። አሁን በራስ መተማመኔ በጣም ጨምሯል። ለሀገሬ ከዚህ በኋላ ብዙ መስራት እፈልጋለው። በተደጋጋሚም ለመጠራት በጣም ጠንክሬ መስራት አለብኝ። ትልልቅ ተጫዋቾች የሰሩትን ታሪክ መስራት እፈልጋለው። ይህንም ከፈጣሪ ጋር አሳካዋለው ብዬ አስባለው።”