አዲስ አዳጊው ሻሸመኔ ከተማ ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ቢሾፍቱ ላይ እየከወኑ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች በክረምቱ አዳዲስ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ በኋላ የነባሮችንም ውል በማራዘም ዝግጅታቸውን የቀጠሉ ሲሆን አሁን ደግሞ ቡድኑን ለማጠናከር ፊታቸውን ወደ ውጪ ሀገር በማዞር የሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቃቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል።
የመጀመሪያው የክለቡ አዲሱ ዜጋ ፈራሚ የዩጋንዳ ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂው ሳይዲ ኬኒ ነው። የ23 ዓመቱ የግብ ዘብ በሀገሩ ክለቦች ኤስ ሲ ቪላ እና ቡል ክለቦች ቆይታን ካደረገ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሻሸመኔ ከተማ አድርጓል።
ክለቡን የተቀላቀለው ሌላኛው የውጪ ዜጋ የሙከራ ዕድል ተሰጥቶት በአግባቡ በማጠናቀቁ ክለቡን የተቀላቀለው ናይጄሪያዊው አማካይ ሚካኤል ኔልሰን ነው። በሀገሩ ናይጄሪያ በፕሪምየር ሊግ እና በታችኛው ዲቪዚዮን ክለቦች ማለትም ሬሞ ስታርስ ፣ ካስቴና ዩናይትድ ፣ ኤልካኒየም ዋሪየርስ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በቫንደርዘር በተባለ ክለብ ተጫውቶ አሳልፎ ሻሸመኔን ተቀላቅሏል።