ሻሸመኔ ከተማ የሁለት ተከላካዮችን ዝውውር አጠናቋል

የሊጉ አዲስ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ አካቷል።

በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ የሚመሩት እና በቢሾፍቱ ከተማ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመያዝ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ሳምንታትን ያስቆጠሩት ሻሸመኔ ከተማዎች የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቃቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ከፈራሚዎቹ አንዱ ተከላካዩ የአብስራ ሙሉጌታ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን እስከ ዋናው ድረስ በመጫወት እግርኳስን ከጀመረ በኋላ በመቀጠል በጅማ አባ ጅፋር እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በመቻል ቆይታን ያደረገ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዓመት መዳረሻው ሻሸመኔ ሆኗል።

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ተከላካይ ተመስገን ተስፋዬ ሆኗል። ተጫዋቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ ቡራዩ ከተማ ፣ ወሎ ኮምቦልቻ ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ሶዶ ከተማ ተጫዋች በ2014 አጋማሽ ኢትዮጵያ መድንን ተቀላቅሎ በክለቡ እስካለፈው ዓመት ድረስ ከተጫወተ በኋላ ወደ ሻሸመኔ አምርቷል።