ከቀናት በፊት ለሙከራ ወደ ግብፅ ያቀናው ዮሴፍ ታረቀኝ ያለበት ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ዩሴፍ ታረቀኝ አረብ ኮንትራክተር ክለብ ባመቻቸለት የሙከራ ዕድል ምክንያት ከሳምንታት በፊት ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ግብፅ ማቅናቱን ሶከር ኢትዮጵያ መዘገቧ ይታወሳል። አሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት ደግሞ የነበረውን የሙከራ ቆይታ በአግባቡ መጠቀሙን እና ክለቡም በዩሴፍ ታረቀኝ እንቅስቃሴ ደስተኛ በመሆኑ የግብፅ ሊግ የዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ ሦስት ቀናት በፊት ለሁለት ዓመት ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየቱን አውቀናል። ሆኖም የሙከራ ዕድል የሰጠው አረብ ኮንትራክተር ለዮሴፍ ህጋዊ ባለቤት ለሆነው (የሦስት ዓመት ውል ላለው) አዳማ ከተማ የውል ማፍረሻ ክፍያ በቀጥታ ለመፈፀም አቅም እንደሌለው እና በነፃ ዝውውር ዩሴፍን ለመውሰድ እንደሚፈልግ ለአደማ ከተማ በኢሜል ደብዳቤ አስገብቷል።
ለክለቡ ኢሜል መላኩን ያረጋገጥን ሲሆን በዚህ ዙርያ የዩሴፍ ህጋዊ ባለቤት የሆነው አዳማ ከተማ አረብ ኮንትራክተር ክለብ የቀረበውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ በጉዳዩ ዙርያ ዛሬ ውይይት አድርጎ የመጨረሻውን ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዮሴፍ በትናትው የዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምድ በሰራበት ወቅት ስታዲየም ተገኝቶ የተመለከተ እና ከቀድሞ የቡድን አጋሮቹ ጋር ፎቶ የተነሳ ሲሆን ዛሬ ምሽት በJune 30 አየር ኃይል ስታዲየም ብሔራዊ ቡድኑ የሚያደርገውን ጨዋታ ይታደማል ተብሎ ይጠበቃል።