በትግራይ ዋንጫ ፍፃሜ መቐለ 70 እንደርታ ስሑል ሽረን በመለያ ምት በመርታት የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
ትግራይ ክልል እግርኳስ ፌደሬሽን እና ሸቶ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን በጋራ ያዘጋጁት የትግራይ ዋንጫ ዛሬ በመቐለ 70 እንደርታ እና ስሑል ሽረ የፍፃሜ ጨዋታ ተጠናቋል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ፍልሚያ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ስሑል ሽረዎች ሲሆኑ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ያስቆጠረው ደግሞ በውድድሩ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ናትናኤል ተክሉ ነው።
በሁለተኛው አጋማሽ ሽረዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ማፈግፈጋቸውን ተከትሎ አጥቅተው የተጫወቱት መቐለ 70 እንደርታዎች ለሰባ ያህል ደቂቃ ከተመሩ በኋላ በዘጠኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። የግቧ ባለቤትም ከወዲሁ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ግዙፉ አጥቂ ዮሴፍ ደስታ ነው። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ጨዋታው ወደ መለያ ምት ካመራ በኋላም መቐለ 70 እንደርታዎች ስድስት ለአምስት በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
በአስራ አንድ ክለቦች መካከል በተካሄደው ውድድር አማኑኤል ልዑል ኮከብ ተጫዋች ፣ ክብሮም አፅብሃ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ፣ ጎይትኦም ኃይለ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ሲሸለሙ አማኑኤል ኃይለስላሴ ኮከብ ዋና ዳኛ እንዲሁም ጥዑማይ ካሕሱ ኮከብ ረዳት ዳኛ ሆነው ተሸልሟል።