ፈረሰኞቹ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ የሚካሄድበት ስታዲየም የት እንደሆነ ለማጣራት ሞክረናል።
በመጀመርያው ዙር የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ከኤም ኬኤም’ን አሸንፈው ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከግብፁ አል አህሊ ጋር ለሚያደርጉት የሜዳቸው ላይ ጨዋታ የሚካሄድበት ስቴድየም ለመምረጥ በሂደት ላይ ከቆዩ በኋላ ጨዋታው በፈርዖኖቹ ምድር ለማካሄድ ለካፍ ማሳወቃቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።
በካፍ መመርያ መሰረት እስከ ሴፕተምበር አንድ ድረስ ስታድየም የመምረጥ ዕድል የነበራቸው ፈረሰኞቹ ጨዋታውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመካሄዱ ነገር እንዲሁም ያለ ደጋፊ በዝግ ሊካሄድ ይችላል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ በካይሮ አል ሳላም ስቴድየም ላይ ለማድረግ ከውሳኔ እንደደረሱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በተያያዘም ከወዲሁም በካይሮ ለሚያካሂዱት ጨዋታ የትኬት ሽያጭ፣ የቴሌቭዥን መብት እና ሎሎች ተያያዥ ሥራዎች ለማሳለጥ ከአንድ ተቋም ጋር በንግግር ላይ መሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜናም የአዲስ አበባ መስተዳድር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጨዋታው ወደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲመለስ ለክለቡ አመራሮች ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል። ሆኖም የካፍ ስታዲየም የመምረጫ ቀነ ገደብ ሴፕተምበር አንድ መጠናቀቁን ተከትሎ ጨዋታው ወደ አዲስ አበባ የሚመለስበት ዕድል ጠባብ እንደሆነ እየተሰማ ይገኛል።