👉 “በወዳጅነት ጨዋታ ብናገባም በነጥብ ጨዋታዎች ሙከራ እናደርግ ነበር..
👉 “በግብፅ ተፈርቶ የነበረውን በብዙ ጎል የመቆጠር ስጋት በልጆቹ የስነ ልቦና ….
👉 “ከንአን ማርክነህ እና ጋቶች ፓኖም በግብፅ ክለቦች የሚታዩበት ዕድል ተፈጥሯል…
👉 “ብዙ ጊዜ የኋላ ኳስ እንጫወታለን ይባል ነበር። በእኔ የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ግን…
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከግብፅ ጋር ያደረገውን ጨዋታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ጊዜያዊ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዳንኤል ገብረማርያም ማብራሪያ ሰጥተዋል። አሰልጣኙ በመግቢያ ንግግራቸው ግብፅ ከደረሱ በኋላ ባሉት አጭር የሁለት ቀናት ልምምድ ሰርተው ለጨዋታው እንደተዛገጁ በማንሳት መቶ ፐርሰንት የተዘጋጀነውን ያህል ባይሆንም አጥጋቢ በሆነ መልኩ መጫወታቸውን እና በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የተገኙ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን ገልፀዋል። ያገኙትን ዕድል አለመጠቀም እና በነበረው መጠነኛ ክፍተት አንድ ጎል እንዳስተናገዱ አውስተው ተፈርቶ የነበረውን በብዙ ጎል የመቆጠር ስጋት በተጫዋቾቹ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማክሸፋቸውን ሆኖም አንድ ጎል ተቆጥሮባቸው መሸነፋቸውን አብራርተዋል። በዚህ ጨዋታ የሚማሩበትን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖችን ማየታቸውን ፣ ለቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ ይጠቅማል የሚሉትን መረጃ በመስጠት እንዳሰቡ ፣ ታሪካዊ ባላንጣን ግብፅን በሜዳዋ ጫና ውስጥ ከተው ከሰማንያ ደቂቃ በኋላ ኳሱን ለማዘግየት የተለያዩ ነገሮችን ለማድረግ ማሰባቸው እንግዳ እንደሆነባቸው በመገረም ተናግረዋል። በአጠቃላይ ያገኙትን አጋጣሚ ቢጠቀሙ ኖሮ ጨዋታውን ሦስት ለአንድ አልያም ሁለት ለአንድ አሸንፈው ህዝባቸውን በውጤቱ ደስተኛ ለማድረግ የተቻላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን በመግለፅ የመግቢያ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
በመቀጠል ከመገናኛ ብዙኃን የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎችን ከአሰልጣኙ ምላሽ ጋር በተከታይነት እንዲህ አቅርበነዋል።
በጊዜያዊነት ቡድኑን በተረከቡት ጊዜ አንስቶ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስለሰሯቸው ሥራዎች…
“ማንኛውም አሰልጣኝ ወደ ኃላፊነት ሲመጣ የራሱን ሀሳብ ይዞ ይመጣል። እግርኳስ ማለት በማጥቃት እና በመከላከል ከሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ከመጀመርያው፣ ከሁለተኛው እንዲሁም በሦስተኛው ጨዋታ በቡድኑ ውስጥ መሻሻሎች አይቻለው። የኔ የጨዋታ ዘይቤ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጋጣሚ ሳይሆን ተጠንቶ እና ተሰርቶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መጫወት እና የግብ ዕድሎችን መሞከር የሚችል ብሔራዊ ቡድን መሆኑን ማየት ተችሏል። በቀጣይ የሚመጣው አካል ይሄንን ይሰራል ብዬ አስባለው። ብዙ ጊዜ የኋላ ኳስ እንጫወታለን ይባል ነበር። በእኔ የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ግን ይህ ሀሳብ አልነበረም። ረጃጅም ኳሶችን ያላበዛ ፣ መካከለኛ እና አጫጭር ኳሶችን እየተጫወተ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ሜዳ ቆይታ እያደረገ ፣ በራስ ሜዳ ላለመቆየት የሚያስብ ነበር። እንዳያችሁት እኔ ከያዝኩት ጀምሮ የማጥቃት ፍላጎት ያለው፣ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ለመግባት ፍላጎት ያለው ፣ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር ነበር። በወዳጅነት ጨዋታ ብናገባም በነጥብ ጨዋታዎች ሙከራ እናደርግ ነበር። ይህ መደረጉ በራሱ አንድ ለውጥ እና እድገት ነው። በአጠቃላይ በቀጣይ በሰነድ የሚቀመጥ መረጃ እንደሚኖር ማንም የሚመጣ አሰልጣኝ በልጆቹ አቅም ላይ ቢሰራ ጥሩ መሆኑን ይችላል። ከንዓን እና ጋቶች ፓኖም በግብፅ ክለቦች ታይተዋል እየተነጋገሩም ነው። ሄደውም የሚታዩበት ዕድል ተፈጥሯል። ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ጨዋታ እየተለወጠ መምጣቱን ፣ መከላከል ብቻ ሳይሆን ማጥቃት መከላከል እንደሆነ በመከላከል የምናባክነውን ጉልበት በማጥቃት ተጋጣሚዎች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል እንዳይወጡ በማድረግ ማጥቃት እንደሚገባ ተማምነን ጨዋታውን አድርገናል። በአጠቃላይ በቆይታዬ የራሴን ሀሳብ ለመተግበር ችያለሁ ብዬ አስባለው።”
ስለ ምኞት ደበበ…
“ምኞት በቴሌግራም ነው የወባ ህመም ላይ መሆኑን ማስረጃውን የላከው። ይህ ማስረጃ እንደደረሰን ቅድሚያ ለተጫዋቾች ጤንነት ነው የምንሰጠው። ተጫዋቹ ወባ እንዳለበት ለአራት ቀን በቀላል ልምምድ እንደሚያቆየው ተናገረ፣ እኛ ደግሞ ከፍ ባለ ልምምድ ስለምንሰራ ይህ ደግሞ ሊጎዳው ስለሚችል፣ ማስረጃውም ይሄን ስለሚል ልጁ በሰጠን ትክክለኛ ማስረጃ መሰረት ከብሔራዊ ቡድን ሊቀር ችሏል። ስለዚህ አንድ ተጫዋችን ላስመረምረው የምችለው እኔ በብሔራዊ ቡድን በማሰራው ልምምድ የተጎዳ ከሆነ ነው። በክለብ ደረጃ የተጎዳን ተጫዋች ብሔራዊ ቡድኑ ኃለፊነቱን ወስዶ ጥልቅ ምርመራ አያደርግም። ልምምድ ከክለቡ ጋር ሰርቶ ይሆናል። ይህን ራሱን ጠይቆ የሚመልሰው ይሆናል። በእኔ በኩል መረጃ አቅርቧል በዚህም መሰረት ከብሔራዊ ቡድኑ ሳይካተት ቀርቷል።”
ስለ ቀጣይ ቆይታ እና ስለሚመጣው አሰልጣኝ ፍንጭ ካለ…
“በእኔ ቆይታ ዙርያ ወደ ግብፅ ከመሄዴ በፊት አሳውቄለሁ። የግብፅ ጨዋታ የመጨረሻዬ መሆኑን ከዚህ ውጭ ያለውን ፌዴሬሽኑን መጠየቅ ይገባል። በቀጣይ ስለሚመጣው አሰልጣኝ ፍላጎት እስካለው ድረስ ምክረ ሀሳብ መስጠት እንደሚቻል። ግን እዚህ ጋር እንዲህ ነው እንዲህ ነው ተብሎ ይገለፃል ብዬ አላስብም። ነገር ግን እኔ ሁለት ጨዋታዎችን ነው የመራሁት በሁለት ጨዋታዎች ያየኋቸውን ምክረ ሀሳቦች ደረጃውን በጠበቀ ተፅፎ ይሰጣል። ይህ መነሻ ነው የሚመጣው አሰልጣኝ ራሱ ከሚከተለው ፍልስፍና ከመነሻ ሀሳቡ ጋር አንድ አድርጎ ይሰራል ብለን እናስባለን። ከአሰልጣኝ ቅጥር ጋር ተያይዞ ቴክኒክ ዳሬክተር የሥራ ድርሻ አይደለም። የማማከር ሥራ ሊሰራ ግን ይችላል። እርሱም እስከ ተጠየቀ ድረስ ዛሬ ላይ እከሌ ሊመጣ ይሆን ይችላል ብሎ መመለስ ያስቸግራል። ነገር ግን በፈጠነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፌዴሬሽኑ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።”
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የተጫዋቾቹ ፍላጎት…
“በእኔ ምልከታ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የተጫዋቾቹ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ ነው ስል ልምድ ያላቸውም ታዳጊዎች በሜዳ ላይ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ለተመልካች መልስ የሰጠነው ብዬ አስባለው። በአሜሪካ የወዳጅነት ጨዋታም ሆነ ከማላዊ እና ከግብፅ ጋር ስንጫወት ፈፅሞ ያላየኋቸው መጠነኛ ለውጥ የመጡበት ነው። ወደ ፊት የብሔራዊ ቡድን ማልያ መልበስ የምንቸገርበት ጊዜ ይመጣል። የብሔራዊ ቡድን ማልያ መልበስ እንደቀላል የየሚቆጠር አይመስለኝም። ለምን ታዳጊዎችን እያየን ዕድል የምንሰጥ ከሆነ ወጣቶቹ ልምድ ካላቸው እየተማሩ ከሄዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መለያ መልበስ ክብሩ እየቀነሰ አይሄድም። ማንኛውም ተጫዋች ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ይፈልጋል። እኔም እንደ ባለሙያ የመጨረሻ ግቤ ለሀገር መስራት ነው። እኔ በነበረኝ ቆይታ በልጆቹ ያየሁት ነገር ጥሩ እና በመከባበር የነበረ ቆይታ ነው ያሳለፍኩት።”