ከ17 ዓመታት በኋላ ከተጫዋችነት ዘመኑ የተገለለው ግብ ጠባቂ በይፋ የወልቂጤ ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባል በመሆን ተሹሟል።
በአዲሱ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መሪነት በሀዋሳ ከተማ ሀሮኒ ሆቴል መቀመጫቸውን አድርገው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመያዝ እየሰሩ የሚገኙት እና በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ የሚካፈሉት ወልቂጤ ከተማዎች ረዘም ላሉ ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በግብ ጠባቂነት ተጫውቶ ያሳለፈውን ቢኒያም ሀብታሙን (ኦሼ) የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አድርገው ሾመዋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ለሙገር ሲሚንቶ ፣ ዳሽን ቢራ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም በግብ ጠባቂነት ተጫውቶ ያሳለፈው ቢኒያም ሀብታሙ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ ክለብ አቃቂ ቃሊቲ ተጫውቷል። አሰልጣኙ እስከ ተጠናቀቀው ዓመት ድረስ ላለፉት 17 ዓመታት ሲጫወት ከቆየ በኋላ ራሱን ከእግርኳስ በማግለል በሀዋሳ ከተማ አብሮ የተጫወተውን የአሁኑ የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ጥሪ ተቀብሎ የወልቂጤ ከተማ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል።