“ቡድናችን ውስጥ ያለው የማሸነፍ ስነልቦና እጅግ ከፍ ያለ ነው”
“ተጫዋቾቻችን የነበረንን የጨዋታ ዕቅድ በትክክል ሜዳው ላይ ተግብረውታል ብዬ አስባለሁ”
“በዕለቱ የነበረው ዳኝነት እጅግ የሚያስደስት ነበር። እንዲህ ዓይነት ፍትሐዊነት ያለው ዳኝነት ሲኖር በጣም ጥሩ ነው”
“ቀጣይ ጨዋታችን ፈታኝ እንደሚሆን እንገምታለን ነገር ግን ግብ ሳናስተናግድ መሄዳችንን እንደ አንድ ዕድል እንቆጥረዋለን”
ባህርዳር ከተማ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ክለብ አፍሪካን በሀብታሙ ታደሰ ግቦች 2-0 ከረታ በኋላ የጣና ሞገዶቹ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታው እንደታየው ጠንካራ ጨዋታ ነው። ተጋጣሚያችን ክለብ አፍሪካ ጠንካራ ነው ፤ ስብስቡ በአፍሪካ መድረክ ትልቅ ልምድ ያለው ክለብ ነው። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቻምፒዮን የሆነ ክለብ ነው። በኮንፌዴሬሽንም እንደዚሁ ብዙ ውድድሮችን ያካሄደ በጣም ከፍተኛ ልምድ ያለው በኤዢያ ካፕም የሚሳተፍ ቡድን ነው እና እንዳያችሁት በሜዳው ላይ የነበረው ጨዋታ ቀላል የሚባል አይደለም። ተጫዋቾቻችን በነበራቸው ቁርጠኝነት ያላቸውን 100% በሜዳ ላይ በመስጠት እጅግ ጣፋጭ የሆነ ድል አስመዝግበናል። በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ። ነገር ግን የዛሬው ጨዋታ ደግሞ ብዙ የሚሰጠን ነገር አለ ፣ ብዙ ተምረንበታል ብዬ አስባለሁ። በቀጣይም ፈታኝ ጨዋታ እንደሚጠብቀን እንገምታለን ፤ ነገር ግን ግብ ሳይቆጠርብን መሄዳችንን እንደ አንድ ዕድል እንቆጥረዋለን እና ጨዋታው እጅግ በጣም ጥሩ ነበር።”
ስለተከተሉት የጨዋታ መንገድ እና ስለ አለልኝ አዘነ ሚና…
“ጨዋታውን እንዳየነው ከታክቲካል አተገባበር አኳያ እኛ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ኳስን አደራጅተን ስንወጣ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚኖረን ቅርፅ 3-1-6 ነው የሚሆነው። ነገር ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድብን እነሱም ደግሞ የሚጫወቱት አጨዋወት በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ስለምናውቅ አለልኝ ያን ኳስ እንዲከላከል እና ለተከላካዮቹ ሽፋን እንዲሰጥ ሞክረናል። በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንደታየው ሁልጊዜም የአማካይ ክፍላችን ላይ ሁልጊዜም አምስት ተጫዋቾች ይኖሩናል። ያን የመሃል ክፍል ተጠጋግተን ለመዝጋት የሞከርነው። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ለተከላካይ ሽፋን የሚሰጥ አንድ የመስመር ተከላካይ ይኖረናል። አለልኝ ግን የማጥቃት እና የመከላከል ሚዛን ጠብቆ ሁልጊዜም ከአጥቂ አማካይ ጀርባ ያለውን ቦታ እየጠበቀ እንዲያጠቃ ነው ዒላማ አድርገን ወደ ሜዳ የገባነው። የነበረንን የጨዋታ ዕቅድ በትክክል ሜዳው ላይ ተግብረውታል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም አይታችሁ ከሆነ አለልኝ ተደጋጋሚ ወደ ጎል ሙከራዎችን ያደረገበት ሁኔታ ነበር። አፈግፍገን አይደለም የተጫወትነው ፤ ማጥቃት ላይ መሠረት አድርገን ለመጫወት ነው የሞከርነው ግን እንደተባለው አለልኝ ኃላፊነቱ ድርብ ነው የነበረው። ለተከላካይ ሽፋን መስጠት በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ ማጥቃቱን ለማሳለጥ ትልቅ ጉልበት ነበር እና ጨዋታው ይሄ መልክ ነበረው። ነገር ግን ተጋጣሚያችን ክለብ አፍሪካ ጠንካራ ክለብ ነው ዛሬም እዚህ ሜዳ ላይ ያየነው ጠንካራውን ክለብ አፍሪካ ነው። በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ረጃጅም ኳሶች እና ኃይል የቀላቀሉ ጨዋታዎችንም ይጫወታሉ። የጠበቅነው ን ነው ያደረጉት ሰዓት በማባከን ፣ ንክኪዎች ላይ ረጅም ሰዓት በመውሰድ ፣ ዳኛው ላይም ጫና በማሳደር ጨዋታው ላይ አንድ ነገር ለመውሰድ ጥረት ያደርጉ ነበር። እጅግ በጣም የገረመኝ ከዕረፍት ወደ ሜዳ ልንገባ እዚህ መልበሻ ክፍል ላይ አሰልጣኞቹ ዳኛው ላይ ተፅዕኖ ያሳድሩ ነበር። ገና ሜዳ ውስጥ ገብቶ ግብ ጠባቂው ሰዓት ሊያባክን ይችላል እና ካልተነገረልን ፤ ይሄ የኛን ግብ ጠባቂ ጫና ውስጥ ለመክተት ነበር። ያንን ለመከላከል ጥረት አድርገናል። ሆኖም ግን በዕለቱ የነበረነው ዳኝነት እጅግ የሚያስደስት ነበር። እንዲህ ዓይነት ፍትሐዊነት ያለው ዳኝነት ሲኖር በጣም ጥሩ ነው። እና የነሱ ጫና በሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳም ውጪ ካላቸው ልምድ በመነጨ ዳኛው ላይ ጫና ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። እንደ አጠቃላይ ክለቡን በጠበቅነው ልክ አግኝተነዋል። ነገር ግን የክለቡ ትልቅነት እንዳለ ሆኖ የኛ ተጫዋቾች ቁርጠኝነት እና ያስመዘገቡት ውጤት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ክለብ አፍሪካ በአፍሪካ መድረክ ባለው ተሳትፎ ከእኛ እጅግ የላቀ ነው። አይታችሁ ከሆነ የማሸነፍ ንጻሬዎች ተቀምጠው ነበር። በእኛ ሜዳ ላይም ሆኖ ወደ 74% የማሸነፍ ግምት የተሰጠው ለክለብ አፍሪካን ነበር። ይሄን ታሪክ ቀይረናል ይሄ እጅግ የሚያስደስት ነው። መረጃዎች ይለዋወጣሉ ከእነሱ ሜዳም የተሰጠው ግምት ክለብ አፍሪካን እንደሚያሸንፍ ነው። ይህ ግን ለእኛ ትልቅ ግብዓት ሆኖን በቀጣይም ጨዋታ የተሻለ ነገር ለማሳየት እንሞክራለን። ብዙ ጫናዎች እንደሚጠብቁን እንገምታለን። ከፈጣሪ ጋር የተሻለ ነገር እናሳካለን ፤ ላሳካነው ውጤት ፈጣሪ ከፊታችን ሆኖ አግዞናል እና ፈጣሪን አመሠግናለሁ።”
ስለ ማሸነፍ ስነልቦናቸው…
“ባህርዳር ከተማ እንግዲህ በዓመቱም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የሚታወቅበት አንዱ የማሸነፍ ስነልቦናው ከፍ ያለ ቡድን ነው። ተጫዋቾቹ ለለበሱት ማልያ ታምነው 100% ያላቸውን ሜዳ ላይ ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉ ተጫዋቾች ናቸው። ታክቲካል ዲስፕሊን አተገባበራቸውም እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። እርግጥ ነው እግርኳስ ሁሌም በማሸነፍ ውስጥም የምናርማቸው እና የምናሳድጋቸው ክፍተቶች ይኖራሉ። ምናልባትም በዛሬው ጨዋታ እንደፈጠርነው ዕድል ወይም ደሞ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ጫና ፈጥረን እንደመጫወታችን ያገኘናቸውን የግብ ዕድሎች በተረጋጋ ሁኔታ መጠቀም ብንችል ኖሮ ውጤቱ ከዚህ የተሻለ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ። ይህን ስል ግን የተገኘው ውጤት ዝቅተኛ ነው እያልኩ አይደለም። ግቦችን ጨምረን ጨዋታውን እዚህ ጨርሰን መውጣት እንችል ነበር የሚል ስሜቱ አለኝ። እንደ አጠቃላይ ላይ ግን ቡድናችን ውስጥ ያለው የማሸነፍ ስነልቦና እጅግ ከፍ ያለ ነው ፤ ከጨዋታ ጨዋታ እያደገ የመጣ ነው። አሁንም ደግሞ እንደምታዩት በዚህ ኢንተርናሽናል መድረክ የመጀመሪያ ተሳትፏችንን አዛምን አሸንፈን አልፈናል ፤ አሁን ደግሞ የገጠመን የሰሜን አፍሪካ ክለብ የሆነው ክለብ አፍሪካ ነው። እሱንም በዚህ መልኩ በሜዳችን ላይ ግብ ሳይቆጠርብን አሸንፈን መውጣታችን የተጫዋቾቻችን ስነልቦና ላይ የሚጨምረው ነገር ከፍ ያለ ነው። ይህንን የአሸናፊነት ስነልቦና ተላብሰን በቀሪዎቹ ጊዜያቶች ደግሞ በክፍተቶቻችን ላይ ሠርተን የመልሱ ጨዋታ ላይ የተሻለ ነገር ለማስመዝገብ ጥረት እናደርጋለን።”
ስለ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ብቃት እና ባለፈው ጨዋታ ስላልተሰለፈበት ምክንያት…
“ፔፔ ሰይዶ ልምድ ያለው ግብ ጠባቂ ነው። ባለፉት ጊዜያቶች ከሀዲያ ክለብ ጋር ያለው ኮንትራት የሚጠናቀቀው ዘግይቶ ስለነበር ፤ ነገር ግን ሊያግዙን ይገባ ነበር በዚሁ አጋጣሚ እንደ ሀገርም ካሰብነው ፔፔ ሰይዶን በመጀመሪያው ጨዋታም ማግኘት እንችል ነበር። ነገር ግን አዛም ላይ የተጠቀምነው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስም እጅግ በጣም የሚያስደንቅ ነበር ፤ አሁን ለተገኘንበት ውጤትም የአላዛር ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። በዚህ በኩል በጣም ዕድለኞች ነን አላዛር ወደፊት ለብሔራዊ ቡድናችንም ግብዓት የሚሆን ትልቅ አቅም ያለው ግብ ጠባቂ ነው። እሱን ነበር የተጠቀምነው። በዛሬው ጨዋታ ደግሞ ረጃጅም ኳሶች እንደሚጠቀሙ ከመሥመር የሚላኩ ኳሶችን ፣ ከቅጣት ምት የሚመጡ ኳሶችን እናውቅ ስለነበር ባገኘናቸው ፊልሞች ፔፔ ሰይዶን አስቀድመናል ለዛሬው ጨዋታ ፤ በትክክልም ደግሞ ልምዱን በሜዳ ላይ አሳይቶ ቡድኑን ግብ ሳይቆጠርበት አስጠብቆ ወጥቷል። በዚህ አጋጣሚ ለነበረው ብቃት ትልቅ አድናቆት አለኝ።”