የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ አሸንፈዋል።
ክለቦች ራሳቸውን የሚፈትሹበት የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ተስተናግደው ወላይታ ድቻን ከዩጋንዳው ኪያንዳ ቦይስ ያገናኘው መርሀግብር ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ጨዋታ ድቻን ባለ ድል ያደረገ ውጤት ተመዝግቦበታል። ወላይታ ድቻዎች በአንድ ሁለት ቅብብል በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ በአንፃሩ የመስመር አጨዋወት የተከተሉት ኪያንዳዎች ጥረታቸው እምብዛም ነበረ ማለት ይቻላል። 23ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የታየው አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ከቀኝ በኩል የደረሰው ኳስ ከመረቡ አሳርፎት ቡድኑን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። በአጋማሹ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ወደ ራሳቸው ያደረጉት ድቻዎች ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መነካቷን ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ቢኒያም ፍቅሬ ለክለቡም ለራሱም ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።
አጋማሹ ሊቋጭ ሲቃረብ ተከላካዩ ኬኔዲ ከበደ ራሱ ላይ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 2ለ1 ሆኗል። ከዕረፍት ተመልሶ በቀጠለው ጨዋታ ኪያንዳ ቦይስ ወደ ጨዋታ ቅኝት ራሳቸውን ባስገቡበት ወቅት የኪንዳ ቦይሱ ካልውሌ ፍራንክ ከወላይታ ድቻው አስናቀ አምታታው ጋር ግጭት አስተናግዷል። ካልውሌ ምላስ በመዋጡ ሜዳ ላይ ህክምና ተደርጎለታል። የሲዳማ ቡና እና የሀዋሳ ከተማ ፊዚዮቴራፒስቶቹ ብሩክ ደበበ እና ሂርፓ ፋኖ ለተጫዋቹ ወደ ሜዳ በመግባት ህክምና ከሰጡት በኋላ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቶ ተመልሷል። ጨዋታው ከ12 ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ ሲቀጥል አብነት ደምሴ ለድቻ ኪኮዚ አምብሮሴ ለኪያንዳ ቦይስ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው በድቻ 3ለ2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ ዘግየት ብሎ ጀምሯል። ተመጣጣኝ ፉክክሮችን ያስመለከት ተቀዳሚው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ የክለቡ ጋናዊ አጥቂ ሚካኤል አፖር መሐል ለመሐል ሾልካ የደረሰችውን ኳስ ሳማኪ መረብ ላይ አሳርፏት ሲዳማን መሪ አድርጓል። ከጎሏ መልስ በተደራጀ መልኩ ወደ መስመር አጋድለው መጫወትን የጀመሩት ፋሲሎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሲዳማ የግብ ክልል አለምብርሀን ይግዛው በጥልቀት ገብቶ ሲመታ ፓሮም ፓጆም የተፋውን ቃልኪዳን ዘላለም አስቆጥሮት ጨዋታውን አቻ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ ፋሲል ከነማዎች ጥሩ በሆኑበት አስር ደቂቃዎች ውስጥ በአምሳሉ ጥላሁን የቅጣት ምት ግብ 2ለ1 ሆነዋል። ዝናባማ በነበረው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና በተሻለ አቀራረብ ላይ ሆኖ ቢገኝም ኳስን ከመረብ በማገናኘቱ ግን አልተሳካለትም። የፋሲሉ አምሳሉ ጥላሁን ከዳኛ በፈጠረው ሰጣገባ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ፓሮም ፓጆም በአንጻሩ ከግብ ክልል ውጪ ኳስን በእጅ በመንካቱ ሁለቱም በተመሳሳይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል። ፋሲልም 2ለ1 ጨዋታውን አሸንፎ ወጥቷል።