የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው መቻል ከወልቂጤ ያለ ጎል ሲፈፅሙ ሀዋሳ ድሬዳዋን አሸንፏል።
አራተኛ ቀኑን በያዘው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ በምድብ ሁለት የሚገኙ ቡድኖችን ጨዋታቸውን አከናውነዋል። አስቀድሞ ወልቂጤ ከተማን ከመቻል ያገናኘው ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን የታየበት መርሀግብር ነበር። በርከት ያሉ ንክኪዎች መሐል ሜዳ ላይ አመዝነው የተመለከትንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎሎችን አይቆጠሩበት እንጂ እንደ ፉክክር ላቅ ያሉ ሁነቶችን አስተውለናል። በመጨረሻም ጨዋታው ግቦች ሳያስመለክተን ያለ ጎል ተቋጭቷል።
በመቀጠል ሀዋሳ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ሀዋሳን ከምድብ ማለፉን ያረጋገጠበትን ውጤት አስመዝግቧል። ቀዝቀዝ ያሉ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች በተወዘተሩበት ጨዋታ ሀዋሳዎች ከተሻጋሪ ኳሶች ግቦችን ለማስቆጠር ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው በሽግግር አጨዋወት አቀራረባቸው አድርገው ተስተውሏል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱለይማን ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻማ እዮብ ዓለማየሁ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብነት ለዎጧታል።
ኳሱ ወደ ግብነት ተለውጣለች ወይስ አልተለወጠችም በሚል አወዛጋቢ ጉዳዮች የነበሩ ቢሆንም በዕለቱ ረዳት ዳኛ አማካኝነት ግቧ ፀድቃለች። ጨዋታው 36ኛ ደቂቃ ላይ እንደደረሰ በመልሶ ማጥቃት እዮብ ዓለማየሁ ለራሱም ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አክሏል። ቀዳሚው የጨዋታ አጋማሽ ሊገባደድ በጭማሪው ላይ ሲያን ሱልጣን ከሳጥን ውጪ ፂሆን መርዕድ መረብ ላይ አሳርፎ አጋማሹ በ2-1 ተገባዷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ቢቀጥልም ሜዳ ላይ ከሚታዩ እንቅስቃሴዎች ውጪ የጎሉ አልያም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን ሳያስመለክተን በ2ለ1 ተቋጭቷል።